ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ እንዲካሄድ ሚናችንን እናጠናክራለን - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ እንዲካሄድ ሚናችንን እናጠናክራለን
አዳማ ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ በማድረግ ረገድ ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመገናኛ ብዙሃንና ሲቪክ ማህበራት የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ገለጹ።
ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙሃን ሚና በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ከተሳተፉት የመገናኛ ብዙሃን ሀላፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መሳፍንት ተፈራ፣ በምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ትልቅ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም መገናኛ ብዙሃን ምርጫው ዴሞክራሲያዊነቱን በጠበቀ መልኩ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም በኢትዮጵያ ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት የሚጥል እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ-ምግባርን ባከበረ መልኩ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቁመው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎች የምርጫ ተዋንያን የሚያደርጉት ጥረት በመገናኛ ብዙሃን ከተደገፈ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊነቱን የጠበቀ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል አንስተው ለዚሁ ስኬት ሚዲያቸው ሚናውን እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ መገናኛ ብዙሃን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መለሰ ሰንበታ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙሃን መርህን መሰረት አድርገው መስራታቸው ምርጫውን ስኬታማ ያደርገዋል ብለዋል።
የዘንድሮ ምርጫ ነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ በማድረግ ረገድ መገናኛ ብዙሀን ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቁመው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በበኩላቸው፤ የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ሂደቱ ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ነጻ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊነቱን የጠበቀ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የሲቪክ ማህበራትና የመገናኛ ብዙሀን ድርሻ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በተለይም የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ነጻ ሆነው በምርጫ ዙሪያ ስራ እንዲሰሩ እድል የፈጠረላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።