ቀጥታ፡

በቅመማ ቅመም ምርት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እየተስፋፋ ነው

ቴፒ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ በቅመማ ቅመም ምርት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የምርት ዝግጅት ሂደትን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ። 

ማዕከሉ የእርድ ምርትን ለገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን ልማዳዊ አሰራር የሚያስቀር አዲስ ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሮች አስተዋውቋል።


 

የእርድ ምርትን በባህላዊ መንገድ ለማዘጋጀት የሚደረገው የመቀቀል ሂደት ከፍተኛ የእንጨት፣ የውሃ፣ የጊዜና የጉልበት ብክነትን የሚያስከትል እንደሆነ ተገልጿል።

የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ደረጀ ቱሉ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ባደረገው የምርምር ሥራ ያስተዋወቀው አዲስ ቴክኖሎጂ የምርቱን ጥራት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ነው። 


 

በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ምርት ለማቅረብ ጥራት ትልቅ ትርጉም እንዳለው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ አዲሱ የእርድ ማዘጋጃ ማሽን ጊዜና ጉልበትን በእጅጉ የሚቆጥብ መሆኑን አስረድተዋል።

የቅመማ ቅመም ምርቶችን በብሔራዊ ደረጃ የሚያስተባብረው ይህ ማዕከል፤ የእርድ ሰብልን በክልሉ በስፋት ማስተዋወቁን ገልጾ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ የማሰራጨት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በማዕከሉ የቅመማ ቅመም ምርት ብሔራዊ አስተባባሪና ተመራማሪ የሆኑት አቡኪያ ጌቱ በበኩላቸው፤ አዲሱ የእርድ መክተፊያ ማሽን ከዚህ ቀደም ሦስት ሳምንታት ይፈጅ የነበረውን የምርት ዝግጅት ጊዜ ወደ 5 ቀናት ዝቅ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በላብራቶሪ በተደረገ ፍተሻ በማሽኑ የተዘጋጀው ምርት የተሻለ የጥራት ደረጃ መያዙ መረጋገጡንና ይህም ለሀገር ውስጥና ለዓለም ገበያ ከባዕድ ነገሮች የጸዳ ምርት ለማቅረብ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

የሸካ ዞን ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዳምሰገድ ኃይለኢየሱስ ፤ በዞኑ ካለው ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ የእርድ ማሳ፣ በዓመት ከ20 ሺህ ቶን በላይ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ ተናግረዋል። 

ማዕከሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ከማቅረብ ባለፈ፣ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቁ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ፤ አርሶ አደሮች ተደራጅተው ማሽኑን መጠቀም የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮችም፤ ነባሩ የእርድ ዝግጅት ሂደት የማገዶ፣ የውሃ እና የጉልበት ብክነት ስለሚያስከትል እስካሁን ከምርቱ ተገቢውን ጥቅም እንዳላገኙ ገልጸዋል። 


 

በተጨማሪም የተቀቀለው እርድ ደርቆ ለገበያ እስኪበቃ ረጅም ጊዜ ይወስድ እንደነበር አስታውሰው፤ ማዕከሉ ያስተዋወቀውን ማሽን በመጠቀም ምርታቸውን በቀላሉ አዘጋጅተው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለገበያ ለማቅረብ ትልቅ ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የእርድ ምርት ለምግብ ዝግጅት፣ ለአልባሳት ማቅለሚያና ለፊት መዋቢያዎች ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ያለው የቅመማ ቅመም ዓይነት መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም