ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቁጥር 3 የበጎነት መንደር የተገነባውን ባለ አምስት ወለል ህንጻ ለተጠቃሚዎች አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቁጥር 3 የበጎነት መንደር የተገነባውን ባለ አምስት ወለል ህንጻ ለተጠቃሚዎች አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ገብስ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ቁጥር 3 የበጎነት መንደር የተገነባውን 44 የመኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ያሉት ባለ አምስት ወለል ህንጻ ለተጠቃሚዎች አስተላልፈዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ገብስ ተራ ቀደም ብሎ እጅግ የተጎሳቆለ እና ለመኖር ምቹ ያልሆነና ባረጁ እና በደቀቁ ቤቶች የተሞላ ነበር ብለዋል፡፡
እንዲሁም በተደጋጋሚ በእሳት አደጋ የሚጠቃ ፣ ለአቅመ ደካሞች እናቶች የማብሰያና የመጸዳጃ አገልግሎት አስቸጋሪ የነበረበት መንደር እንደነበርም አስታውሰዋል።
በዚህ መንደር የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 377 የመኖሪያ ቤቶች ያላቸው 5 ህንጻዎችን መገንባት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ነዋሪዎቻችንም ከዛ አስከፊ አኗኗር ተላቀው ክብራቸውን በሚመጥን ፅዱ፥ ዘመናዊ አኗኗር የሚፈጥር፥ ልጆች ቦርቀዉ የሚጫወቱበት እና ደረጃውን በጠበቀ መኖሪያ መንደር እንዲኖሩ በማድረጋችን በጣም ደስ ብሎናል ሲሉም ገልጸዋል።
በዚህ የበጎነት መንደር ግንባታ ላይ በክትትል እና ድጋፍ አስተዋጽኦ ላደረጉ አመራሮች እንዲሁም ልበ ቀና ባለሀብቶች በገንዘባቸው ላደረጉት ድጋፍ ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል።