በዞኑ የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታን ከማስፋፋት ጎን ለጎን አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታን ከማስፋፋት ጎን ለጎን አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ትኩረት ተደርጓል
መቱ ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ በኢሉባቦር ዞን የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ማሻሻል ትኩረት መደረጉን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
በኢሉባቦር ዞን በበጀት ዓመቱ የተገነቡ 831 የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ክፍት የማድረግ መርሃ ግብር በሀሉ ወረዳ ተጀምሯል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አስተዳደሩ ለሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት የሚሰራ መሆኑን በተጨባጭ ስራዎች እያሳየ ነው።
በዞኑ በትልቅ በጀት የሚሰሩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን በብዛትና በጥራት ለአገልግሎት በማብቃት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በዚህም ዓመት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች የሚመልሱ፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎችን የሚፈቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረግ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ከመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ ጎን ለጎን የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች የሚጠናከሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ለምረቃ የበቁት ፕሮጀክቶችም የአስተዳደር ሕንጻዎች፣ ድልድዮች፣ የጤና ተቋማት፣ መንገዶች፣ የሶላር ኃይል ማመንጫ፣ የመጠጥ ውሃና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ፣ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የበርካታ ፕሮጀክቶች ግንባታ መካሄዱን አስታውሰዋል።
ፕሮጀክቶቹ የልማትና የአገልግሎት ተደራሽነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀሉ ወረዳ ነዋሪዎች ለአገልግሎት እየበቁ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ያለውን አቅም የሚያሳድጉ፤ የሕብረተሰቡንም ማሕበራዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአስተዳደር ሕንጻው ብዙ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በአንድ ሕንጻ ውስጥ የሚሰበስብ እንደመሆኑ አገልግሎት ለማግኘት የሚጠይቀውን ድካም የሚቀንስ መሆኑን ተናግረዋል።