ሶስተኛው ዙር የክለቦች ቦክስ ሻምፒዮና መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሶስተኛው ዙር የክለቦች ቦክስ ሻምፒዮና መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የተዘጋጀው ሶስተኛው ዙር የክለቦች ቦክስ ሻምፒዮና በራስ ኃይሉ ስፖርትና ስልጠና ማዕከል ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች ከ12 ክለቦች የተወጣጡ 126 ቦክሰኞች ተሳታፊ ሆነዋል።
ሻምፒዮናው ለስፖርተኞች ተከታታይነት ያለው የውድድር እድልን ለማመቻቸት፣ በብሔራዊ ደረጃ ሀገርን ወክለው የሚወዳደሩ ብቁ ስፖርተኞችን ለመመልመልና ለመምረጥ ዓላማ ያደረገ ነው።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ መነቃቃት እየታየበት ላለው የካራቴ፣ ማርሻል አርት እና ኤምኤምኤ (MMA) ስፖርት ዘርፎች፤ ብቁ ስፖርተኞችን ከሻምፒዮናው በመመልመል ተጠቃሚ ማድረጉ የውድድሩ ሌላኛው ግብ ነው።
የሶስተኛው ዙር የክለቦች ቦክስ ሻምፒዮና ውድድር ለአንድ ሳምንት እንደሚቆይ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሻምፒዮናው በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ ነው። ሁለት ሻምፒዮናዎች አስቀድመው በአዲስ አበባ ተደርገዋል።
የመጨረሻው ውድድር ከአንድ ወር በኋላ ይከናወናል።
የአራቱ ውድድሮች አጠቃላይ ውጤት ተደምሮ በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ክለቦች ይለያሉ።