ቀጥታ፡

ክልሉን የሰላም፣ የልማትና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ የህዝቡን አቅም አቀናጅቶ መጠቀም ይገባል

ጋቼኖ ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የሰላም፣ የልማትና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ የህዝቡን አቅም አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ፣ ዳሞት ፑላሳ ወረዳዎች እና ሻንቶ ከተማ የተገነቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃው ላይ እንደገለጹት፤ ክልሉን የሰላም፣ የልማትና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ የህዝቡን አቅም አቀናጅቶ መጠቀም ይገባል።

የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ዛሬ በወላይታ ዞን በዳሞት ጋሌና በዳሞት ፑላሳ ወረዳዎች እንዲሁም በሻንቶ ከተማ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የዚሁ አካል መሆናቸውን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለፉት 9 ወራት 275 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወልደ ተስፋዬ ናቸው።


 

ዛሬ የተመረቀው የ15 ኪሎ ሜትር መንገድ በሻንቶ ከተማ፣ በዳሞት ፑላሳና በዳሞት ጋሌ ወረዳዎች የሚገኙ ቀበሌያትን የሚያገናኝ ነው ብለዋል፡፡ 

የሀርቶ ቆንጦላ ጫራቄ ተንጠልጣይ ድልድይ ደግሞ የዳሞት ጋሌና የዱጉና ፋንጎ ወረዳዎች ከ22 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው፤ በዞኑ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለአገልግሎት ክፍት በመደረጋቸው የህዝቡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

ለአብነትም የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት ግንባታ ህዝቡ በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት እንዲያገኝ ማገዙን ጠቁመዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ በመንገድና ድልድይ ማጣት ሁለቱ ወረዳዎች ተለያይተው እንደቆዩ ተናግረዋል።

አሁን መንግስት ችግሩ እንዲፈታ በማድረጉ የጤና አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ በቀላሉ ወደ ገበያ ሄዶ ለመገበያየት እንደቻሉም ገልጸዋል፡፡ 


 

ከዚህ ቀደም መድኃኒት ለመግዛት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ርቀው ይጓዙ እንደነበርም ተናግረዋል።

መድኃኒት ቤት በአቅራቢያቸው በመገንባቱ መድኃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ እና በቅርበት ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም