በክልሉ ለህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እየበቁ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እየበቁ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ
ሰመራ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦በአፋር ክልል ለህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት እየበቁ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።
ገቢ ረሱና ኸሪ ረሱ ዞኖችን እንዲሁም ወረዳዎችን ለማገናኘት የሚያስችሉ የጠጠር መንገዶችና ድልድይ በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እንዳሉት፤ መንግስት ለህብረተሰቡ ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል።
''ዛሬ ያስመርቅናቸው መንገዶችና ድልድይ ለረጅም ዘመናት በመንገድ ዕጦት ምክንያት ለተለያዩ ወጪዎች ተዳርጎ የቆየውን ህብረተሰብ በቅርብ ለማገናኘት የተቻለበት ነው'' ብለዋል።
ይህ መንገድ ህብረተሰቡ ሲያነሳው የነበረውን ጥያቄ መመለስ የተቻለበት እና የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት መሆኑን ገልፀው መሰል ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህ እንዲሳካ ያደረገውን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ ለመንገዱ መጠናቀቅ ላደረገው ተሳትፎ አመስግነዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ መንግስት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
''የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የልማት ማዕከል ለማድረግ የመንገድ ልማት አስፈላጊ መሆኑን ተረድተን ውጤታማ ስራዎች እያከናወንን እንገኛለን" ብለዋል።
አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከዚህ በበለጠ ተጠቃሚነቱ እንዲጨምር በትብብር የሚሰሩ ተግባራት የሚጠናከሩ መሆኑንም አክለዋል።
በዛሬው ዕለት ለተመረቁት የጠጠር መንገዶችና ድልድይ ስራ 433 ሚሊዮን ብር በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት ወጪ የተደረገባቸው መሆኑ ተመላክቷል።