ቀጥታ፡

የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየተከናወነ ያለው ተግባር ይጠናከራል-እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ግንቦት ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ ከለውጡ ወዲህ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) አስታወቁ።

የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በጉራጌ ዞን ከምሁር አክሊል ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ህዝባዊ ውይይት አካሄደዋል።


 

በወቅቱም የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ የክልሉ መንግስት ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል።

ለተነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ማህበረሰቡን ባሳተፈ አግባብ ምላሽ እንደሚሰጥም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

የወረዳውን የመስህብ ስፍራዎች እና ቅርሶች በአግባቡ በማልማትና በማስተዋወቅ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲሁም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማስፋፋት ከባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራም ገልጸዋል።


 

የምሁር ኢየሱስ ገዳም እና በዙሪያው ያሉ ቅርሶችን ለማልማት የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ከሁሉም እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ባለሀብቶች በገዳሙ ዙሪያ የእንግዶች ማረፊያ በመገንባት ለዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና  አስተዳደሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው በአካባቢው፤ ያለውን ፀጋና ሀብት በመጠቀም የህብረተሰቡን ኑሮ በማሻሻል ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡


 

ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራን የሚያሰፉ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው አመልክተዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ብስራት ገብሩ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ የአካባቢን ጸጋ በማልማት የህዝቡን  ዘላቂ  ተጠቃሚነት  ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።


 

በወረዳው የህዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ በጤና ዘርፍ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በውይይት መደረኩ ላይ የተሳተፉ ከፍተኛ የክልሉና የዞኑ አመራሮች በዞኑ ምሁር አክሊል ወረዳ የሚገኘውን ታሪካዊው የምሁር እየሱስ ገዳምን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም