ቀጥታ፡

በክልሉ በለውጡ ዓመታት የህዝብን የልማት ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል 

ወንሾ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል በለውጡ ዓመታት የህዝብን የልማት ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ የተገነቡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


 

በምረቃው ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ የህዝብን የልማት ጥያቄ መሰረት ያደረጉ ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት  ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው፣ በልማት ሥራዎቹ የህብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ዛሬ የተመረቁ የልማት ፕሮጀክቶች የክልሉ መንግስትና በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች በቅንጅት ያስመዘገቡት ውጤት ነው ብለዋል።

የልማት ፕሮጀክቶቹ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሳለጥ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚፈቱ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የወንሾ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልዴ ዩምራ በበኩላቸው፤ በወረዳው የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውና ህዝቡም የተሳተፉባቸው ናቸው ብለዋል።


 

ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ከበቁ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ መካከል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት፣ የወረዳ አስተዳደር ሕንጻ  እና ሌሎች አገልግሎት የሚያሳልጡ የመንግስት ተቋማት እንደሚገኙበትም አመልክተዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን በሂደት የመመለስ አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ሽታዬ እሳቱ፤ የለውጡ መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር ባከናወናቸው የልማት ፕሮጀክቶች ህዝቡ ተጠቃሚነቱ እየተረጋገጠ መጥቷል።

ዛሬ የተመረቁ ፕሮጀክቶችም አገልግሎትን የሚያሳልጡና የወረዳውን እድገት የሚያፋጥኑ ናቸው ብለዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ፣ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አብርሃም ማርሻሎ እንዲሁም ሌሎች የክልሉና የፌደራል መንግስት የሥራ ሃላፊዎችና የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም