ቀጥታ፡

ከተረጂነት ወጥተን በጀመርነው የገቢ ማስገኛ ሥራ ተጠቃሚ ሆነናል-አርሶ አደሮች

ሀዋሳ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ከምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተረጂነት ወጥተው በጀመሩት የገቢ ማስገኛ ሥራ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ለሌሎችም እንደተረፉ አርሶ አደሮች ገለጹ።

ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመተባበር "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ በሃዋሳ ባዘጋጀው መድረክ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት፤ በገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ መሰማራታቸው ተጠቃሚ አድርጓቸዋል።  

ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና መርሀግብር ታቅፈው በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ህይወታቸውን ይመሩ እንደነበር አስታውሰው፣  በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ውጤታማ ከመሆን ባለፈ ለሌሎች መትረፍ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሙዲ ሀሰን እንዳሉት፤ ለዓመታት በፕሮግራሙ ታቅፈው በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ሕይወታቸውን ሲመሩ ቆይተዋል።

በአካባቢያችን 65 ነዋሪዎች በመርሀግብሩ ድጋፍ ሲደረግልን ቆይተናል ያሉት አርሶ አደሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ15ቱ በማህበር ተደራጅተው በንብ ማነብ እና በቅመማ ቅመም ልማት ሥራ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

የንብ ማነብ ሥራውን በ25 ዘመናዊና ባህላዊ ቀፎ ታግዘው እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው፣ በአንድ ተኩል ሄክታር ማሳ ላይም ሮዝመሪ በማልማት 300 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ካይሻ ኤርጌቾ፤ አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ለዓመታት በፕሮግራሙ በተደረገላቸው ድጋፍ ህይወታቸውን ሲመሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብ በጀመሩት የሱቅ እና አነስተኛ ግብርና ሥራ ገቢያቸውን በማሳደግ ከእርዳታ ሙሉ በሙሉ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

በሀላባ ዞን የሲምቢጣ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገረመው መሀመድ፤ በቀበሌያቸው በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ምክንያት ለዓመታት ከቀዬያቸው በመፈናቀል ለተረጂነት ተዳርገው እንደነበር አስታውሰዋል።

በተደረገላቸው ድጋፍ ታግዘው በተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ መሰማራታቸውን ገልጸው፣ በዚህም ከተረጂነት ወጥተው በተለያየ አካባቢ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ሀብት ማፍራታቸውን ጠቅሰዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ ነዋሪው ወጣት አርሶ አደር ታሪኩ ታደሰ በበኩሉ እንዳለው፣ ቀደም ሲል ምንም አይነት ገቢ ስላልነበረው በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሰርቶ በሚያገኘው አነስተኛ ገቢ ይተዳደር ነበር።

በአሁኑ ወቅት በቡና እና በሥራ ሥር ተክሎች ልማት ተሰማርቶ ገቢውን በማሳደግ 2 ሚሊዮን ብር ሀብት ማፍራቱን ተናግሯል።  

በእዚህም ከእርዳታ ተላቆ ከራሱ ባለፈ በአቅራቢያው አቅመ ደካማ ቤተሰብ እያገዘ መሆኑንም ገልጿል።

ከሲዳማ ዞን ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱላ ቀበሌ የነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ዴቢቴ ናሮ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በመርሀግብሩ ያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብ በጀመሩት የዶሮና ፍየል እርባታ ሥራ ከእርዳታ ተላቅቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም ያረቧቸውን ፍየሎች ለሌሎች በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም