ቀጥታ፡

የምርጫው ሂደት የሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረትን ከማፅናት ባለፈ የዴሞክራሲ ልምምድ ሁነኛ ማሳያ ነው

አዳማ ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት የሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረትን ከማፅናት ባለፈ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ልምምድ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የመንግስት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለፁ። 

ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙሃን ሚና በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።


 

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የምርጫ ሂደት ብሄራዊ ጥቅምን ለማሳካት የሚደረግ ጥረትና የዴሞክራሲ ልምምድ ነው።

በዚሁ መሰረት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ እስካሁን በስኬት መቀጠሉን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግና ማሳካት የሚቻለው በተደመረ አቅም መትጋት ሲቻል መሆኑን ገልፀው ምርጫው አንዱ የብሄራዊ ጥቅም መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።

የብሄራዊ ጥቅምና የሀገር ሉአላዊነት ጉዳይ ያለ ልዩነት የምንሰራበት የጋራ አጀንዳችን ነው ያሉት አቶ ተስፋሁን ለዚህም የሚዲያ ሚና ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግረዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፣ በምርጫ የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በዚሁ መሰረትም የሲቪል ማህበራት ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት በላቀ ቁርጠኝነት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን በገለልተኝነት በማገልገልና ማህበረሰብን በማንቃት ጠንካራ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ ሲሉም አክለዋል ። 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ፣ መገናኛ ብዙሃን ህግና አሰራርን ተከትለው እንዲያገለግሉ ባለስልጣኑ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።


 

በእስካሁኑ የምርጫ ሂደትም መገናኛ ብዙሃኑ ገንቢ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል። 

በመድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮች በምርጫ ሂደቱ የህዝቡ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን ገልፀው ሚዲያውም በዚሁ ልክ ለመስራት እየጣረ መሆኑን አመልክተዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ለምርጫው ስኬታማነት በብቃት መስራት እንዳለባቸው አንስተው ሚዛናዊና ጥልቅ እይታ ያለው ዘገባ ተደራሽ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም