ቀጥታ፡

የጋራ ምክር ቤቱ ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት ሂደት የድርሻውን እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት በመገንባት ሂደት ውስጥ ድርሻውን በላቀ ሁኔታ እየተወጣ መሆኑን ገለጸ።

የጋራ ምክር ቤቱ 14ኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ የበጀት ዓመቱ የ10 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።


 

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ ፤ ምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያፋጥኑ እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።

ባለፉት አሥር ወራት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረኮችን ከማዘጋጀት ባለፈ፣ የፓርቲዎችን የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያሳድጉ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ የመምከር ባህል፣ ተቀራራቢ አቋም መያዝ፣ እርስ በርስ መደማመጥ እና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት የሆኑ ተግባራትን ጨምሮ ቀደም ሲል ያልነበሩ ለውጦች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

አባል ፓርቲዎች የምክር ቤቱን የሥራ ጥንካሬ ለማስቀጠልና የሚታዩ ድክመቶችን ለመቅረፍ፣ እንዲሁም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የዛሬው ውይይት አስፈላጊነትም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲዳብር የጋራ ትብብርን ለማጠናከር ነው ብለዋል።

የምክር ቤቱ ጸሐፊ አቶ ታሪኩ ድንበሩ በበኩላቸው፤ የጋራ ምክር ቤቱ በተለይም የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና የተረጋጋ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ቆይቷል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እና ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት እንዲጣል ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በፓርቲዎች መካከል የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር እና ችግሮች ሲያጋጥሙም በውይይትና በንግግር እንዲፈቱ ምክር ቤቱ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም መድረኩ በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያለው የእርስ በርስ መተማመን መንፈስ እንዲጎለብት ያደርጋል ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱም ባለፉት 10 ወራት ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ነፃና የዴሞክራሲ ተምሳሌት በሆነ መንገድ እንዲከናወን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም