ለሀገርና ለሕዝብ ይበጃል ያልነውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል-የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገርና ለሕዝብ ይበጃል ያልነውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል-የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች
ባህርዳር፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር እድገት ይሰራል ያልነውን ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት የድምጽ መስጫውን ቀን በጉጉት እየጠበቅን ነው ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሀብታሙ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዜግነት ድርሻቸውን እየተወጡ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን ከሚያደርጉት የምረጡኝ ቅስቀሳና ክርክር በቂ እውቀት በማግኘት ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቼያለሁ ነው ያሉት።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ በለጠ ደረበ በበኩላቸው፤ ከጎረቤቶቻቸው እና ከአካባቢው ነዋሪ ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም ነቅተው በመጠበቅ መጪው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል።
ህገ-መንግስቱ ያጎናፀፈኝን መብት በመጠቀምም በወሰድኩት የመራጭነት ካርድ የሀገርን አንድነት፣ ልማትና ዕድገት ያፋጥናል ብዬ ላመንኩበት ፓርቲ ድምጼን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
በምርጫ ካርዱ አገርን ያሻግራል ብሎ ላመነበት ፓርቲ በነፃነት ድምጹን ለመስጠት መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት ትልቅሰው አንሙት ነው።
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን ነው የገለጸው፡፡