ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በመኸር አዝመራ እስካሁን 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር የመሬት ዝግጅት ተደርጓል

ጅማ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በመኸር አዝመራ ለማልማት ከታቀደው መሬት እስካሁን 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር የመሬት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በዛሬው ዕለት የክልሉ ግብርና ቢሮ አመራሮች እና የጅማ ዞን የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዞኑ ቦተር ጦላይ ወረዳ ለመኸር አዝመራ እርሻ የተዘጋጀ መሬትን በበቆሎ ዘር የመሸፈን ሥራ ተጀምሯል።


 

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ በዘንድሮው የመኸር አዝመራ 11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። 

በእስካሁኑ ሂደትም በመኸር አዝመራ ለማልማት ከታቀደው አጠቃላይ መሬት 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር የሚሆነው መሬት ተዘጋጅቷል ብለዋል።


 

ዘንድሮ የግብርና ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ ቀደም ብለው እየቀረቡ በመሆናቸው በመኸር የተሻለ ውጤት እንደሚገኝ ተስፋ ተጥሏል ነው ያሉት።

በክልሉ ግብርናን በሜካናይዜሽን ለማስፋፋት ባለፉት ዓመታት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፣ በዚህ ዓመት ብቻ 1 ሺህ 200 ትራክተሮች ለክልሉ አርሶ አደሮች መድረሳቸውን ገልጸዋል። 

በዚህ ወቅትም አጠቃላይ በክልሉ ከ11 ሺህ በላይ ትራክተሮች የግብርና ሥራውን በማቀላጠፍ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ለዘንድሮ እርሻ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከታቀደው 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 7 ሚሊየኑ ወደ ክልሉ የገባ ሲሆን፣ 3 ሚሊየን የሚሆነው ተሰራጭቷል ብለዋል።

የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዩሱፍ ሻሮ በዞኑ ለአርሶ አደሮች ቀደም ብሎ የግብርና ግብዓቶች እንዲቀርቡ መደረጉን ተናግረው፣ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ 883 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዷል ብለዋል። 


 

አጠቃላይ ከሚለማው መሬት ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ዘር የሚለማ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የቦቶር ጦላይ ወረዳ አርሶ አደር ከበደ ታየ በ7 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ የማልማት ሥራ መጀመራቸውን ገልጸው፣ በኩታ ገጠም ማረሳቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።


 

አርሶ አደሩ ዘንድሮ በቂ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በማግኘታቸው ብዙ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር ኡመር ቃሲም ከዚህ ቀደም በኩታገጠም በማልማት ከአንድ ሄክታር 75 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረው በትራክተር ታግዘው በማረስ መሬታቸውን በዘር የመሸፈን ስራ መጀመራቸውን ገልፀዋል።

በዘንድሮ እርሻ ለአርሶ አደሮች አስፈላጊ ሙያዊ እገዛ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም