ፓርቲው የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ተግባራት አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲው የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ተግባራት አከናውኗል
አምቦ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በሌሎችም ዘርፎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ተግባራት ማከናወኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ በምዕራብ ሸዋ ዞን እና በአምቦ ከተማ አስተዳደር የምርጫ ቅስቀሳ አካሄደ።
በቅስቀሳ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ እንደገለጹት፤ ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት የሕዝቡን ሕይወት የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎች አከናውኗል።
በተጨማሪም የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሠራው ሥራ ሁሉን አቀፍ ውጤት እየተገኘ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም በኦሮሚያ ክልል በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በሌሎችም ዘርፎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚችሉ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ፓርቲው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማረጋገጥ፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት እንዲሁም አብሮነት እንዲጠናከር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ እንደገለጹት፤ ብልፅግና ሀገር በቀል የሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን አንግቦ የተነሳ ፓርቲ ነው።
በዞኑ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የክልሉ መንግሥት በቀረጻቸው የልማት ኢኒሼቲቮች አማካኝነት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰፋፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት አምቦን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ብዙ መሠራቱን የገለጹት ደግሞ የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሐጫሉ ገመቹ ናቸው።
ፓርቲው ተጨባጭ የልማት ሥራዎችን በከተማ ግብርና እና በሌሎች ዘርፎች በጥራት መሥራቱን አብራርተዋል።