ከተሞችን በማዘመን የእድገት ምንጭ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞችን በማዘመን የእድገት ምንጭ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው
ደብረ ብርሃን፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞችን በማዘመን ለእድገት መሰረት እንዲሆኑ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር ) ገለጹ፡፡
የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በደብረ ብርሃን ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር ) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግስት ከተሞችን በማዘመን ለኢንቨስትመንት ፣ ለቱሪዝምና ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤት እየተመዘገበባቸው ነው።
በከተሞች ተገንብተው የተጠናቀቁና በመገንባት ላይ ያሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ለምጣኔ ሃብት እድገት መሰረት እየጣሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የአስፋልት መንገድ፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማን ለኢንዱስትሪ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ተመራጭ እንድትሆን ለማድረግም የመሰረተ ልማት ግንባታ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ ከተማዋ ለአምራች ኢንዱስትሪ ያላትን ተመራጭነት በመጠቀም የማምረት አቅምን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለት የተጎበኙትም የሶስት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት፣ ከሁለት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድን ጨምሮ የሶስት ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 56 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ጠቁመው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግንባታን በማጠናቀቅ የኔትወርክ ዝርጋታ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የልማት ፕሮጀክቶቹም በከተማ አስተዳደሩና በነዋሪዎች የጋራ ትብብር እየተገነቡ የሚገኙ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።