ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል
ቃሉ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለፁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በ365 ሚሊዮን ብር የተገነባውን ዲርማ ወንዝ መስኖ ፕሮጀክት ዛሬ መርቀዋል።
በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
በተለይም ግብርናውን በሜካናይዜሽን፣ በቴክኖሎጂና በአዳዲስ አሰራር በማዘመን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለገበያ የሚቀርብ ምርት ለማምረት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ በስፋት እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ይሄን የውሃ ሀብት ለመስኖ ልማት በማዋል ዓመቱን ሙሉ የማምረት ሥራው ይጠናከራል ብለዋል።
ለእዚህም በክልሉ በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በቃሉ ወረዳ ዛሬ የተመረቀው ፕሮጀክትም ለእዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የደዋጨፋ ወረዳን በጋራ የልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉም አክለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የመስኖ መሰረት ልማቶችን በማስፋፋት አርሶ አደሩ ከዝናብ ጠባቂነት ተላቆ በመስኖ ጭምር በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረቱ ውጤት እያስገኘ ነው።
በቃሉ ወረዳ በ365 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀው የመስኖ ፕሮጀክት ከ290 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያስችልና ከ490 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል።
ግንባታው በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁ የመንግስትን ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ የመፈጸም ብቃት ያሳያል ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን፤ በዞኑ የሚገነቡ በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶች ምርታማነትን በማሳደግ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ የተመረቀው የመስኖ ፕሮጀክት አርሶ አደሩ በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ የሚያስችለው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቃሉ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን አህመድ ናቸው።
በምረቃው ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።