ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሰላምና ልማት ይሰራል ያልነውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች

ወልቂጤ፣ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ)፡-በወሰድነው የመራጭነት ካርድ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ይሰራል ያልነውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። 

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በመገናኛ ብዙሃን የተመቻቸላቸውን የዓየር ሰዓት በመጠቀም  ማኒፌስቷቸውን እና አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ለመራጩ ህዘብ በማስተዋወቅና ላይ ናቸው፡፡

በምርጫው ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉራጌ ዞን ነዋሪዎችም በጠቅላላ ምርጫው ለሃገር እና ለህዝብ ዘላቂ ሰላምና ልማትን የሚያስቀጥል ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ማርታ ሽበሺ እንዳሉት በጠቅላላ ምርጫው በንቃት መሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ ወስደው የድምጽ መስጫ ቀኑን በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ፓርቲዎች በብዙሀን መገናኛ እና በተለያዩ አማራጮች እያደረጉት ያለውን የምረጡኝ ቅስቀሳና የሚያቀርቧቸውን የፖሊሲ አማራጮች ሲከታተሉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመለየት እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

ሌላው የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሙባሪክ ጀማል እንዳለው፣ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም ድምጹን ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ለመስጠት ተዘጋጅቷል።

በዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ለፓርቲዎች ምቹ መህዳር መፈጠሩ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉን ገልጾ፣ እሱም ድምጹን ከመሰጠት ባለፈ ለምርጫው ሰላማዊና ፍትሀዊነት የበኩሉን እንደሚወጣም አረጋግጧል። 

የአካባቢው ወጣቶችም በወሰዱት ካርድ ድምጻቸውን ለሚፈልጉት ፓርቲ በነጻነት በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በተግባር እንዲያረጋግጡ የማስገንዘብ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ተናግሯል።

በዞኑ የቸሃ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሙደሲር የሲሩ እንደገለጹት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሀገርን መፃኢ ዕድል ለመወሰንና የተረጋጋ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ በመሆኑ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ተግቶ ይሰራል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

በምርጫው ቀን የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ሀገርን በልማት ያሻግራል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ የተናገሩት ደግሞ በጉራጌ ዞን የምሁር አክሊል ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ዙርያሽ ደሴ ናቸው። 

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስጠብቃል፤ ህዝብንም በሰላምና ልማት ተጠቃሚ ያደርጋል ያልነውን የፖለቲካ ፓርቲ  ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ደግሞ በእኖር ወረዳ የመራጭነት ካርድ የወሰዱት ተናኜ ባድገባ ናቸው፡፡

ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ የሚሰጥበት ቀን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲሆን የጉራጌ ዞን ነዋሪዎችም ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት ዕለቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም