ክትባትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ በማድረግ የበሽታ ወረርሽኞችን የመከላከል አቅምን ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ክትባትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ በማድረግ የበሽታ ወረርሽኞችን የመከላከል አቅምን ማሳደግ ተችሏል
አሶሳ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ ሀገር አቀፍ የክትባት ሽፋንን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ በማድረግ፣ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችንና ወረርሽኞችን የመከላከል አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስቴር "ለእያንዳንዱ ትውልድ ክትባቶች ይሰራሉ" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የአፍሪካ ክትባት ሳምንት ንቅናቄ መድረክ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መዲና አሶሳ ከተማ አካሄደ።
በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች እና የዘርፉ አጋር አካላት ተገኝተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር ስለሺ ጋሮማ በወቅቱ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ መከላከልን መሠረት አድርጎ የተቀረጸው የጤና ፖሊሲ ክትባትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ በማድረግ፣ የበሽታ ወረርሽኞችን አስቀድሞ የመከላከል አቅምን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።
በተለይም ህጻናት መደበኛ ክትባቶችን በተሟላ ሁኔታ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ከተለያዩ ለህልፈትና ለሕመም ከሚዳርጉ በሽታዎች ለመታደግ ትልቅ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ክትባት ሳምንት መከበር ዋና ዓላማም ክትባት ለሁሉም ትውልድ ተደራሽ የሚሆንበትን ዕድል ከመፍጠር ባለፈ፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ስለ ክትባት የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማረም መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የክትባት ተደራሽነት እንዲያድግ የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት አዎንታዊ ለውጥ መታየቱንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የክትባት ስርጭትና ተደራሽነት ከአፍሪካ አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስና አርአያ የሚሆን መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒሴፍ የክትባት ስፔሻሊስት አልማዝ መርደኪዮስ ናቸው።
ቀደም ሲል በክትባት ብቻ በቀላሉ መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች የበርካታ ሕጻናትን ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ ይቀጥፉ እንደነበር ያስታወሱት ስፔሻሊስቷ፤ በአሁኑ ወቅት ግን እንደ ኩፍኝ፣ ፖሊዮ እና ሳንባ ምች ያሉ አስከፊ በሽታዎችን በተደራጀ መልኩ መከላከል የሚያስችል አገራዊ አቅም መፈጠሩን አስታውቋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አብዱልሙኒዬም አልበሽር በበኩላቸው በክልሉ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ ክትባት የመጀመሪያ አማራጭ ተደርጎ እየተሰራበት ነው ብለዋል።
በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ክትባት ያመለጣቸው ህፃናት ክትባት እንዲወስዱ ለማድረግ በየጊዜው ሰፊ የንቅናቄ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።