የከሰም መስኖ ግድብ ማሻሻያ ግንባታ መጠናቀቅ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በዘላቂነት ይቀርፋል-ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የከሰም መስኖ ግድብ ማሻሻያ ግንባታ መጠናቀቅ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በዘላቂነት ይቀርፋል-ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
ሰመራ፣ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦የከሰም መስኖ ግድብ የማሻሻያ ግንባታ መጠናቀቅ ከሚሰጠው ዘላቂ የልማት አገልግሎት ባሻገር፣የአካባቢውን ማህበረሰብ ለዓመታት ሲፈታተን የነበረውን የጎርፍ ስጋት ሊቀርፍ የቻለ ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) አስታወቁ።
የከሰም መስኖ ግድብ የጥገና ማሻሻያ ፕሮጀክት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት በይፋ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
በዚህ ወቅት ሚኒስትር አብረሃም(ዶ/ር) እንዳሉት፥ የከሰም መስኖ ግድብ ቀደም ሲል በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እንደ ትልቅ ስጋት ይታይ ነበር።
ግድቡ ከዚህ ቀደም ይፈጥር ከነበረው የአደጋ ስጋት ተላቆ ለአካባቢው ነዋሪዎች አስተማማኝና ጠቃሚ የልማት መሠረተ-ልማት መሆን የቻለው በተደረገለት ስልታዊ የኢንጂነሪንግ ጥገናና ማሻሻያ አማካኝነት መሆኑን ገልጸዋል።
በአካባቢው ማህበረሰብ የነበረውን የአደጋ ስጋት በመቅረፍ ግድቡን ለታለመለት የመስኖ ልማት ለማዋል ለተከናወነው የጥገናና ማሻሻያ ፕሮጀክትም 2 ቢሊዮን ብር በጀት መውጣቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የከሰም መስኖ ግድብ የውሃ ፍሰት በተመጣጣኝና ቁጥጥር በተደረገበት ሁኔታ እንዲለቀቅ በማድረግ፣ ለአካባቢው የግብርና ሥራዎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ላይ እንዲውል መደረጉን ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እንዳሉት፥ ተጠግኖ ወደ አገልግሎት የገባው ግድቡ ህብረተሰቡን ከስጋት ያዳነ እና በርካታ ጥቅሞች ያሉት ነው።
በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ይስተዋል የነበረውን ስጋት በማስወገድ ረገድ የተከናወነው ሥራ ውጤታማ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የግድቡ ጥገና መጠናቀቅ የማህበረሰቡን የቆየ ጥያቄ የፈታ መሆኑንም ተናግረዋል።