ቀጥታ፡

የቱሪስት መስህብ መዳረሻዎችን የማልማት ስራ ላይ ትኩረት መሰጠቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያበረከተ ነው

ጎንደር ፤ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ)፡-በለውጡ ዓመታት  በጎንደር ከተማ  የተከናወኑ የቱሪስት  መስህብ  ልማቶች  የዘርፉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ  እያሳደጉ መሆኑን  የዘርፉ ምሁራንና የስራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

የጎንደር አብያተ መንግስት ጥገናና እድሳት ጨምሮ የጎርጎራ የኢኮ ሪዞርት ግንባታ የዘርፉን  አቅም አልምቶ መጠቀም እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ መሆኑም ተገልጿል።

በጎንደር ዩንቨርሲቲ የቱሪዝምና ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊና የዘርፉ ተመራማሪ የሺዋስ አቡኔ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ያላትን  የቱሪዝም ሃብት በተገቢው በማልማት ጥቅም ላይ የማዋል ተግባር ተዘንግቶ እንደነበር ያስታውሳሉ።


 

ከለውጡ አመታት ወዲህ ግን መንግስት የቱሪዝም  ጸጋዎችን በማልማትና በማስተዋቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን የማጉላት ስራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአብነትም  የፋሲል አብያተ መንግስትን ጥንታዊና ታሪካዊ ገጽታውን በጠበቀ መልኩ ታድሶና ተጠግኖ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉንና የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት በአዲስ መልክ ማልማት መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተለይም የጣና ሀይቅን ጨምሮ የተለያዮ የተፈጥሮ ጸጋዎች በጎንደርና ሰሜን ተራሮች ከሚገኙ ቅርሶች ጋር እንዲተሳሰሩ መደረጉ  በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻ የመሆን እድልን ያሰፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 ዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም ዘርፉን በእውቀትና በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲመራ ለማስቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥም በመጀመሪያ፣ በ2ኛ እና በ3ኛ ዲግሪ  በርካታ ባለሙያዎች በማፍራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የጎንደርን የቀደመ ስምና ታሪክን  የሚዘክሩ ሰው ሰራሽ  የቱሪስት መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ የዘርፉን ሀገራዊ እድገት ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ መሰራቱን ያነሱት  ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ልማት ቡድን መሪ አቶ አይቸው አዲሱ ናቸው።


 

ለአብነትም  የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት ዛሬ ላይ ታሪኩንና ገናና ስሙን በሚመጥን መንገድ እንደጠገን መደረጉ ታላቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተሰጠው ልዩ ትኩረት እድሳትና ጥገናው የተጠናቀቀው ቤተ መንግስቱ ባለፉት 10 ወራትም አካባቢውን የሚገበኙ  ቱሪስቶች ቁጥር ወደ 5ሺህ ከፍ እንዲል  ማድረጉን ተናግረዋል።

የቱሪስቶቹ ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር በ3 ሺ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመው ይህም  የቱሪስት መዳረሻዎችን በመጠበቅና በማልማት  የተመዘገበ ለውጥ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቅርስ ጥበቃና ልማት ስራው ማህበረሰቡ በዘርፉ ለጎብኝዎች አገልግሎቶችን በመስጠት የሚያገኘው ገቢ እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አመልክተዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም