ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ የንብ ሃብት መጠንን በማሳደግ የማር ምርትና ጥራት እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጾ አድርጓል

ዲላ፤ ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሀገራዊ የንብ ሃብት መጠንን በማሳደግ የማር ምርትና ጥራት እንዲያድግ ጉልህ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የንብ ልማት ማህበር አስታወቀ።

ዓለም አቀፍ የንብ ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ በዲላ ከተማ ሲከበር ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለድርሻ አካላት እንዳሉት ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ለንብ ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

በየዓመቱ የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርም፣ ሀገራዊ የንብ ሃብት መጠንን በመጨመር የማር ምርትና ጥራት እንዲያድግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተገልጿል።

መርሀግብሩ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ ባለፈ የሥነ ምግብ ይዘትን ለማሻሻል ጉልህ አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ የንብ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ነጋሽ በቀና በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ መንግስት ለንብ ሃብት የሰጠው ትኩረት የዘርፉን እምቅ አቅም አውጥቶ ለመጠቀም እያስቻለ ነው። 

በተለይ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርን ጨምሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች የንብ ሃብት መጠንን በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እያገዙ መሆኑን ተናግረዋል።  

የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ከሌማት ትሩፋት ትግበራ ጋር ተዳምሮ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ ባለፈ የማር ምርት ጥራትና ይዘትን አሻሽሏል ብለዋል።

የክልሉን እምቅ የንብ ሃብት ልማት በአግባቡ ለመጠቀም የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊና የእንስሳትና አሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ሃላፊ አባይነህ ከዳ (ዶ/ር) ናቸው።

በተለይ የንብ መንጋ ብዜት ማዕከላትን በማስፋፋትና አርሶ አደሩን በመንደር በማደራጀት በተደረገ የግብዓትና የክህሎት ድጋፍ የዘርፉን ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከ17 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ማር ለገበያ መቅረቡን በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ የአንድነት ንብ ልማት ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ብርቱካን ተስፋዬ በበኩላቸው 12 ሆነው በማህበር በመደራጀት በንብ ልማት ሥራ መሰማራታቸውን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ባለው ከ50 በላይ ዘመናዊና ባህላዊ የንብ ቀፎ በዓመት ከ1 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ማር በማምረት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የማህበሩ አባላት ከራሳቸው ባለፈ ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት ለሌሎች ወጣቶች አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም