በሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች የኢንዱስትሪውን ምርታማነት አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች የኢንዱስትሪውን ምርታማነት አሳድጓል
ሀዋሳ፤ ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ)--በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ማሳደግ እንደተቻለ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመመሪያው ሃላፊ አቶ በሀይሉ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሳደግ ከሀይል አቅርቦት ጋር የሚነሱ ችግሮችንና መሰረተ ልማቶች ለማሟላት በተቀናጀ መንገድ ተሰርቷል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ እስካሁን ድረስ 70 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመግባት ከ9 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፈጠራቸውን ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበትና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትን ኤግዚብሽንና ባዛሮችን በማዘጋጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም ነው አቶ በሀይሉ አመልክተዋል።
የአብርሽና ቤተሰቡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ከድር አህመድ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪው እየገጠሙት ያሉትን ችግሮች በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአስተዳደሩ በኩል የድጋፍና ክትትል ሥርዓት በመጠናከሩ የዓለም አቀፍ ገበያን ደረጃ የሚያሟሉ የቆዳ ምርቶች እያመረቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሀይል አቅርቦት ችግር እየተፈታ መምጣትና ለኢንዱስትሪዎች በተለያያ መንገድ የገበያ ትስስር መፈጠሩ ለውጤታማነቱ የላቀ ድርሻ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ከድር ገለጻ ኢንዱስትሪው በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ወደ 9 ሚሊዮን ብር ያሳደገ ሲሆን ለ107 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
የኦሱ ማሽነሪ ፈጠራዎች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ወጣት በረከት ሀይሉ በበኩሉ ከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪዎችን ማበረታታቱ የማህበረሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የተለያዩ ማሽኖችን በማምረት ለገበያ እንዲያቀርቡ ያገዛቸው መሆኑን ተናግሯል።
በዚህም ድርጅቱ ካፒታሉን እያሳደገ ከመምጣቱ ባለፈ ለ15 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
በመንግስት በኩል የቀረበላቸው የመስሪያና የመሸጫ ቦታ እንዲሁም አስተማማኝ የሀይል አቅርቦት መኖሩ ስራቸውን ውጤታማ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ይህም ድርጅቱ ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን በማምረት በአነስተኛ ዋጋና በላቀ ጥራት ለገበያ ለማቅረብ አንዳስቻለው ጠቁመዋል።
የህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህል እየጎለበተ መምጣቱም ሥራቸውን ለማሳደግ ብርታት እንደሆናቸው ገልጿል።