ቀጥታ፡

በክልሉ ከ261 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ችግኞችን ለመትከል የ ጉድጓድ ቁፋሮ ስራ ተጀምሯል

ባህርዳር ፤ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ከ261 ሺህ ሔክታር በላይ  በሆነ መሬት  ላይ ችግኞችን ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮ ስራ መጀመሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

‎‎በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለፁት የክልሉን የደን ሽፋን ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በመጭው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን በላይ የዋንዛ፣ ወይራ ፣ ዝግባ ፣ ፅድ ፣ አኬሺያ ዲከረንስ፣ ባህር ዛፍ፣ የፍራፍሬና ሌሎች ችግኞችን ለመትከል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የችግኝ ተከላውን በስኬት ለማከናወን እስካሁን 401 ሚሊዮን በላይ ጉድጓዶችን በማስቆፈር ለተከላ ዝግጁ ማድረግ መቻሉን አረጋግጠዋል።

‎‎‎‎በቀጣይም የአረንጓዴ አሻራ ግብን ለማሳካት ተጨማሪ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን የማስቆፈር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ባጠቃላይ በክረምቱ ለሚካሄደው ችግኝ ተከላ 261 ሺህ 297 ሄክታር መሬት ከወዲሁ ተለይቶ የጉድጓድ መቆፈር ስራው እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር መኮነን ልንገር እንደገለጹት ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መጀመሩ  ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎችን መልሰው በደን እንዲሸፈኑ ለማድረግ አስችሏል።

መርሃ ግብሩ ለመኖ ፣ በንብ ማነብና እንስሳት እርባታ እያስገኝ ያለውን ተጠቃሚነት ለማስፋት  በመጭው ክረምት በሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በግልና በወል ቦታዎች ችግኝ ለመትከል ጉድጓዶችን እያዘጋጀን ነው ብለዋል።

የሚተከሉት ችግኞች አያስገኙ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት በየዓመቱ  ችግኞችን እያለማሁ ነው ያሉት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የደራ ወረዳ አርሶ አደር ካሴ መንግስት ናቸው።

በመጭው ክረምት የሚተከሉ ችግኞች ተንከባክበን በማሳደግ ለውጤት ለማብቃት ከወዲሁ ዝግጅት ጀምረናል ነው ያሉት።     

ባለፈው ክረምት በነቃ የህዝብ ተሳትፎ ከተተከለው ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ ችግኞች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው መጽደቁን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም