ቀጥታ፡

‎‎ስማርት ቆጣሪዎች ዘመናዊና ግልጽ አሰራርን በማስፈን የኃይል ብክነትን መቀነስ አስችለዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ) ፡-በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የስማርት ቆጣሪዎች ትግበራ ዘመናዊና ግልጽ አሰራርን በማስፈን የኃይል ብክነትን መቀነስ ማስቻሉን ‎የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በአገልግሎቱ የፖርትፎሊዮ ማኔጅመንት የዲስትሪዩብሽንና አውቶሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ተስፋዬ ሂርጳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አገልግሎቱ አስተማማኝ፣ቀልጣፋ እና ተደራሽ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት የስማርት ቆጣሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡

ለዚህም 500 ሺህ ስማርት ቆጣሪዎችን በመግዛት በሀገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን 160 ሺህ ቆጣሪዎች ተገጥመው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ከተገጠሙት ስማርት ቆጣሪዎች መካከል 140 ሺህ ባለ ነጠላ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ባለ ሶስት ፌዝ መሆናቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋት በቀጣይ 300 ሺህ የደረሱ ስማርት ቆጣሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡

ስማርት ቆጣሪዎች ደንበኞች ያለ አንዳች እንግልት ባሉበት ሆነው ክፍያ መፈጸም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ተጠቃሚዎች ምን ያህል ኃይል እየተጠቀሙ እንደሆነ እንዲረዱ ከማገዙም በላይ የኃይል አጠቃቀማቸውን ተረድተው አላስፈላጊ አጠቃቀምን በመቀነስ ኃይልን መቆጠብ ያስችላል ነው ያሉት።

ከቆጣሪና ከኃይል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የደንበኞችን ቅሬታ ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸው፤ በኃይል አጠቃቀም የመረጃ ንባብ መዘግየትና መሳሳት ተቋሙ ሊያጣ የሚችለውን ገንዘብ ያስቀራል ብለዋል፡፡

ስማርት ቆጣሪዎች ማናቸውንም አይነት የቆጣሪ ማጭበርበር ወይም ያልተፈቀደ ንክኪ በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ቁጥጥር ክፍሉ የማሳወቅ ብቃት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ የኃይል ሥርቆትን ለመከላከል የጀመረውን ሥራ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከፍተኛ የኃይል ሥርጭት በሚያጋጥምበት ወቅት አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ቆጣሪው ኃይል ማገድ የሚያስችል ስርዓት እንዳለው ጠቁመዋል።


 

በምሥራቅ አዲስ አበባ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቁጥር ስምንት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ድሪባ አብዲሳ በበኩላቸው፤ማዕከሉ የነጠላና የባለሶስት ፌዝ ስማርት ቆጣሪዎችን ለነዋሪዎችና ለደንበኞች እየገጠመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስማርት ቆጣሪዎች ቴክኖሎጂ አዲስ መሆኑን በመግለጽ፤ አገልግሎቱን በተመለከተ ለኅብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም