ሲቪክ ማህበራት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚኖራቸውን የክትትልና ድጋፍ ሚና አጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ሲቪክ ማህበራት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚኖራቸውን የክትትልና ድጋፍ ሚና አጠናክረው መቀጠል አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ ሲቪክ ማህበራት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚኖራቸውን የክትትልና ድጋፍ ሚና አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙሃን ሚና” በሚል ርዕስ በጋራ ያዘጋጁት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ለማስገንዘብ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
በመድረኩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ሀላፊዎች እና ጋዜጠኞች ታድመዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ የሲቪክ ማህበራት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚኖራቸውን የክትትልና ድጋፍ ሚና አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ምርጫን ማካሄድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው የሲቪክ ማኅበራት ሚና እጅግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ሲቪል ማህበራት በምርጫ ወቅት ያላቸው ሚና ታዛቢነት ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በኃላፊነትና በባለቤትነት እንዲቆሙ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸውም ነው ያሉት።
በዚህም ማህበራቱ ዜጎች ስለ ምርጫ አስፈላጊነት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማደረግ በኩል ኃላፊነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በምርጫው ሂደት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ማብቃት ላይ በትኩረት ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመው ይህንኑ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን ምርጫውን በተመለከተ በሚሰሯቸው ዘገባዎች ህግን ተከትለው መስራታቸውን ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደቡትን ነጻ የቅስቀሳ እና የማስተዋወቂያ ሰዓት አጠቃቀም ላይ ችግር እንዳልተከሰተ ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን በምርጫ ወቅት በሰላም ግንባታ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ባለስልጣኑ ሲሰራ መቆየቱንና ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በምርጫ ወቅት የሚጠበቁ የስነምግባር መርሆዎች እንዲጠበቁ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የአቅም ግንባታ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ፕሮግራም መሰረት ምርጫውን በተመለከተ የተለያዩ የዘገባ ስራዎችን ለህዝብ ተደራሽ ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።
በዚህም ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሚናቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ከፓናሉ ተሳታፊዎች በምርጫው ወቅት የመገናኛ ብዙሃንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናን የተመለከቱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የተሰነዘሩ ሲሆን በፓናሊስቶቹ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።