በአፋር ክልል የተገነቡ የጠጠር መንገዶችና የብረት ድልድይ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የተገነቡ የጠጠር መንገዶችና የብረት ድልድይ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ
ሰመራ፣ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦በአፋር ክልል በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች መካከል ያለውን የትራንስፖርት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከርና የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ታስበው የተገነቡ የጠጠር መንገዶችና የብረት ድልድይ ፕሮጀክቶች ተመርቀው በይፋ ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።
ፕሮጀክቶቹን መርቀው ወደ ስራ ያስገቡት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባና የመስኖና ቆላማ አካቢዎች ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ናቸው።
በዛሬው ዕለት ከተመረቁት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል የብረት ድልድዩን በውስጡ የያዘው የገቢ እና የኸሪ ራሱ ዞኖችን በዘላቂነት የሚያስተሳስረው የ64 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ፕሮጀክት አንዱ ነው።
ይህ የተመረቀው የመንገድ መሠረተ-ልማት በሁለቱ ዞኖች መካከል ያለውን ትስስር ከማጠናከሩ ባለፈ፣በመካከላቸው የሚገኙትን የገለአሉ እና የሰሙሮቢ ወረዳዎችን በቅርበት የሚያገናኝና የማህበረሰቡን የትራንስፖርት ችግር በከፍተኛ ደረጃ የሚያቃልል መሆኑ ተመላክቷል።
የጠጠር መንገዱና የብረት ድልድዩ 361 ሚሊዮን ብር የወጣበት ሲሆን ከ81 ሺህ በላይ ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ተመላክቷል።
የሀደለኤላ እና ሰሙሮቢ ወረዳዎችን የሚያስተሳስረውና ከ16 ሺህ በላይ ዜጎችን ከወረዳና ከዞን ማዕከላት ጋር የሚያገናኘው የ18 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ፕሮጀክትም ሌላኛው ነው።
አዲስ ለተመረቀው የ18 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ፕሮጀክት 72 ሚሊዮን ብር በጀት የወጣ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ለልማት ሥራዎቹ 433 ሚሊዮን ብር በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት ወጪ መደረጉ ተጠቅሷል።