ቀጥታ፡

በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ ልዑክ በአዘርባጃን የተቀናጀ የከተማ ልማት ፕሮጀክትን ጎበኘ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 12 /2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ የልዑካን ቡድን በአዘርባጃን ያለውን የተቀናጀ የከተማ ልማት ፕሮጀክት ጎብኝቷል።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው፤ አዘርባጃን በአሁኑ ወቅት ካስመዘገበችው ከፍተኛ ዕድገት ጎን ለጎን የከተማ መልሶ ማልማት ሥራዎችን አጠናክራ መቀጠሏን ገልጸዋል።

አሮጌ መንደሮችን በማንሳት የማደስ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን ለይቶ የማልማት ስትራቴጂ እየተከተለች እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዚህም በ16 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁ 50 ሺህ መኖሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ተያያዥ የልማት ሥራዎች በ"Sea Breeze ፕሮጀክት" ሥር በስፋት እየተገነቡ እንደሚገኙና የግሉ ዘርፍም ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት በከፍተኛ ደረጃ እየተሳተፈ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በአዲስ አበባም፣ በየዓመቱ 100 ሺህ ቤቶችን እና ተያያዥ ልማቶችን ለመገንባት ታቅዶ በከፍተኛ ርብርብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

ከተማ አስተዳደሩ ያረጁና የተጎሳቀሉ አካባቢዎችን የመቀየርና የማደስ ሥራዎችን እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋሉ እንደ የጫካ ፕሮጀክት፣ ገላን-ጉራ፣ መሐመድያ መንደር እና አዲስ ቱሞሮ ያሉ አካባቢዎችን በመጠቀም አዲስ ከተማ የመገንባት ያህል ምቹ የልማትና የመኖሪያ ስፍራዎችን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ይህ መጠነ-ሰፊ የቤት ልማትና የከተማ ማደስ እንቅስቃሴ በዋናነት የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለልና መዲናዋን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የታለመ ነው ብለዋል ከንቲባዋ።

በቀጣይነትም በላቀ ጥረትና በልማት ልኅቀት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ግንባር-ቀደም ለማድረግ አበክሮ የመሥራት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም