ቀጥታ፡

የዘንድሮው ምርጫ ሂደት የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎና የዳበረ የዴሞክራሲ ልምምድ የታየበት ነው- ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ

አዳማ፤ ግንቦት 12/2018  (ኢዜአ) ፡-የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎና የዳበረ የዴሞክራሲ ልምምድ የታየበት  መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ ገለፁ። 

"ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙሃን ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው። 


 

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ መድረኩ በሀገር ጉዳይ ላይ የሚመከርበት ትልቅ የሃሳብ ገበታ መሆኑን ገልፀዋል። 

የምርጫ ሂደት ደግሞ የህዝብ የመወሰን አቅምና ልምምድ በተግባር የሚታይበት መሆኑን አንስተው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን አንስተዋል። 


 

በመሆኑም የምርጫው ሂደት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድ እየዳበረ መምጣቱን ያሳየ መሆኑን አንስተው  በስኬት እንዲጠናቀቅ መገናኛ ብዙሃን የላቀ ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል። 

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት መገናኛ ብዙሃን ሚናቸው የላቀ መሆኑን አንስተዋል። 


 

በመሆኑም ለዘንድሮው ምርጫ ስኬታማነት መገናኛ ብዙሀን በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልፀው፣ ለስኬታማነቱ በተደመረ አቅም ይበልጥ በመተባበር መስራት የሚገባን ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል። 

በመድረኩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም