ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በካሳቫና ሌሎች አዋጭ የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ጋምቤላ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ) ፡-በጋምቤላ ክልል በካሳቫና በሌሎች አዋጭ የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የተጀመሩት ተስፋ ሰጪ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

የጋምቤላ ክልል እጅግ ሰፊና  ሊታረስ የሚችል ለም መሬት፣ አመቺ የአየር ንብረት እንዲሁም ከፍተኛ ውሃ ያለው በመሆኑ ለግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ ነው። 

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በክልሉ በስፋት እየተለመደ የመጣው የካሳቫ ምርት፣ ድርቅን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑና ለምግብ ዋስትና ከመዋሉ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ሰፊ ፍላጎት ስላለው በክልሉ ትኩረት ከተሰጣቸው የሰብል ዓይነቶች መካከል አንዱ ነው። 

ክልሉ ይህንን እምቅ አቅም በመጠቀም የሃገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የጸጥታ ሁኔታን ከማስተካከል ባለፈ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የኤሌክትሪክና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን በማስፋፋት ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንደገለጸው በክልሉ በባለሃብቶች የተጀመረውን ዘመናዊ የካሳቫ ልማት ወደ አርሶ አደሮች በማስፋት የምግብ ዋስትናን የማረጋገጡ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሎው ኦቡፕ(ዶ/ር) እንዳሉት ካሳቫን ጨምሮ ለምግብ ፍጆታም ሆኑ ለገበያ አዋጭ የግብርና ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

የክልሉ ህዝብ ቀደም ሲል የካሳቫን ተክል እያመረተ በባህላዊ መንገድ ለምግብነት ሲጠቀም መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በዘርፉ ባለሃብቶችን በማሳተፍ የካሳቫ ልማቱን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ካሳቫ ከሌሎች ስራ ስር አትክልቶች ሁሉ በምርታማነቱ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ተክሉ ለእንጀራና ለዳቦ ዝግጅት ከመዋሉ ባለፈ፣ ለተለያዩ የምግብ ዓይነቶች የሚያገለግል  ሰብል መሆኑን ገልጸዋል።

የካሳቫ ልማት በተለይም እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለተያዘው ብሄራዊ ግብ መሳካት ዓይነተኛ ፋይዳ እንዳለውም ኮሚሽነር ሎው (ዶ/ር) ገልጸዋል።


 

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አቶ አንድሮው ቱት በበኩላቸው የካሳቫ ልማት በክልሉ በሚገኙ ዞኖች በባህላዊ መንገድ ሲከወን መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በዘመናዊ መልኩ በባለሃብት የተጀመረውን የካሳሻ ልማት ወደ አርሶ አደሩ በማስፋት እንደ ሀገር የምግብ ሎዓላዊነትን ለማረጋገጥ የታዘውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በአቦቦ ወረዳ በካሳቫ ኢንቨስትመንት የተሰማራው የአያል ኃላፊነቱ የተወሰነ እርሻ ልማት ድርጅት ተወካይ አቶ ቾቤ ሞላ በሰጡት አስተያየት የካሳቫ ልማት በምርታማነትም ሆነ በገበያ አዋጭ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ካሳቫ ድርቅን የሚቋቋምና በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ከ150 እስከ 200 ኩንታል ምርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ ከአራት ወር ጀምሮ ምርት መስጠት የሚችል ተክል እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት በ50 ሄክታር ማሳ ላይ ልማቱን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይ ዓመት ከ200 ሄክታር በላይ መሬት ልማትና  የካሳቫ ዱቄት ፋብሪካ የመክፈት እቅድ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የካሳቫ ተክል ጋምቤላን ጨምሮ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በአርሶ አደሮች አነስተኛ ማሳዎች ላይ እየተመረተ ለዘመናት ለምግብነት ሲያገለግል የቆየ ሰብል ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም