ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ስኬታማ የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ተሞክሮ ለመውሰድ ፍላጎት አሳይተዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12 /2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ስኬታማ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ትግበራ ተሞክሮ ለመውሰድ ፍላጎት ማሳየታቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ ገለጹ።

በኮትዲቩዋር መዲና አቢጃን በተካሄደው የ"ID4Africa 2026" የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ተሞክርን በማካፈል የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ብቃትና ዕድገት በተግባር ማሳየት ተችሏል፡፡

የ"ID4Africa 2026" ዓመታዊ የአፍሪካ የዲጂታል መታወቂያ ጉባኤ "ከዲጂታል መሠረተ ልማት ወደ ዲጂታል የሕዝብ ሥነ-ምህዳር" በሚል መሪ ሃሳብ  በኮትዲቩዋር መዲና አቢጃን እ.ኤ.አ ከግንቦት 12 እስከ 15 ቀን 2026 ተካሂዷል።

በዚህም በሀገር በቀል አቅም የተገነባው የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ጉባኤው ላይ አድናቆት እንደተቸረውም ተጠቁሟል፡፡

በዚሁ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያስመዘገበችውን ውጤታማ ጉዞና ተሞክሮ አቅርባለች።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ ጉባኤውን አስመልክተው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መድረኩ ኢትዮጵያ የራሷን ተሞክሮ ከማቅረብ ባለፈ ሌሎች ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለ ስራዎቿ አዎንታዊ ምስክርነት የሰጡበት ነው።

ጉባኤው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ብቃትና ዕድገት በተግባር ማሳየት የተቻለበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ከተካሄደው የ“ID4Africa 2025” መድረክ ወዲህ በሀገሪቱ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ረገድ አስደናቂ ለውጥ መመዝገቡን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት የብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ43 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ጠቅሰዋል።

ይህም በየሳምንቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የመመዝገብ ከፍተኛ ብሔራዊ አቅም መፈጠሩን የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽነቱን ከማስፋት ጎን ለጎን፣ ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የማቀናጀት ሥራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል። 

እስካሁን ድረስ በባንክና ፋይናንስ፣ በትምህርት እንዲሁም በጤና መድህን ዘርፎች በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማካተት የቻሉ ወደ 132 የሚጠጉ የአገልግሎት ሥርዓቶች ትስስር መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በራሷ ወጣቶች፣ መሐንዲሶች እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ቁርጠኝነትና በሀገር በቀል ዕውቀት መገንባቷ በጉባኤው ላይ ትልቅ አድናቆት እንዳስገኘላት አስታውቀዋል።

ይህ በራስ አቅም የተመዘገበው ስኬት ከኢትዮጵያ አልፎ እንደ ዛምቢያ እና ሞዛምቢክ ያሉ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለመውሰድና አጋርነት ለመመሥረት ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያሳዩ በር ከፍቷልም ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የቢሊዮን ሕዝብ መለያ ሥርዓት ባለው የሕንዱ አድሃር (Aadhaar) ከፍተኛ ኃላፊዎች ጭምር የሕንድን ሥርዓት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማቀናጀት፣ የሁለቱን አገራት የቴክኖሎጂ ትብብር ለማሳየት ፍላጎት ማቅረባቸውን አክለው ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም