ቀጥታ፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ እየሰራን ነው - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 

አሶሳ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረተሰቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የግንዛቤ ስራ እየሰሩ መሆናቸውን አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ትምህርት እና ግንዛቤ መስጠት ለይ ለሚሰማሩ 169 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እውቅና መስጠቱ ይታወቃል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዕውቅና ከተሰጣቸው ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል አንዱ የቦሮ ሽናሻ ልማት ማህበር ነው።

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አስማማው ዘገዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች  የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡ በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠ ነው።

ማህበሩ በየአካባቢው የህዝብ መድረኮችን በመፍጠር ህብረተሰቡ በምርጫ ላይ ያለውን ግንዛቤ እንዲያሳድግ እና ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ  ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስችል ትምህርት መስጠታቸውን አስታውቀዋል።

ለአብነትም የመራጭነት ካርድ ያላወጡ ዜጎች ካርድ በማውጣት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ሰፊ የንቅናቄ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።

ማህበሩ በቀጣዮቹ ቀናት ህብረተሰቡ ለመራጭነት ያወጣው ካርድ ዋጋ እንዳለውና በድምጽ መስጫ ቀን ተገኝቶ ድምጹን እንዲሰጥ ለማድረግ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሌሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ገለልተኛ በመሆን ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶች ምክርቤት አባል ወጣት ቴዎድሮስ ተክላይ በበኩሉ፤ ምክርቤቱ ወጣቶች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ መድረኮች የግንዛቤ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል።

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ፤ በተለይም ወጣቶች በምርጫው ላይ በመሳተፍ የሀገር ተረካቢ ትውልድ መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብሏል።

በክልሉ የተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶችን በመጠቀም በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች እና የህብረተሰብ ክፍሎች በምርጫው ተሳታፊ እንዲሆኑ በቅንጅት መስራታቸውንም  ወጣት ቴዎድሮስ ገልጿል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም