የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለጥያቄያችን ምላሽ የሰጠ ነው-የወረዳዎቹ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለጥያቄያችን ምላሽ የሰጠ ነው-የወረዳዎቹ ነዋሪዎች
ሠመራ፣ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል ገቢ ረሱ ዞን የዱለቻና አሚበራ ወረዳዎች ነዋሪዎች፤ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት በመጓዝ ያባክኑት የነበረውን ጊዜና ጉልበት እንዳስቀረላቸው ገለጹ።
በወረዳዎቹ የተለያዩ ቀበሌዎች በ109 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር ወጪ በመሰኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት የተገነቡት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብረሃም በላይ(ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ይታወሳል።
የፕሮጀክቶቹን ምረቃ ተከትሎ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ያሲን መሐመድ በአካባቢው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት አራት ሰዓት የደርሶ መልስ ጉዞ የሚወስድ መሆኑን አስታውሰዋል።
በተለይም ሴቶች የችግሩ ሰለባ ሆነው መቆየታቸውን ገልፀው፤ በፕሮጀክቶቹ አማካኝነት የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄያቸው ተመልሶ በደጃቸው እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ አባሂና ሁመድም የፕሮጀክቶቹ መመረቅ በቅርባችን ውሃ ማግኘት አስችሎናል፤ በዚህም ደስተኞች ሁነናል ብለዋል።
ቀድሞ ያልጠራ የጎድጓድ ውሃ ከሩቅ ስፍራ በጀርባችን አዝለን ነበር የምናመጣው፤ አሁን ላይ ውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት ጉዞና ድካም አስቀርቶልናል ብለዋል።
የዱለቻ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የውሃ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ኢነሃባ በበኩላቸው፤ የተገነቡት ፕሮጀክቶች እናቶች ንጹህ ውሃ ለማግኘት ያባክኑት የነበረውን ረጅም ሰዓትና እንግልት ያስቀሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የነበረው የውሃ እጥረት ችግር በመቀረፉ ለሰውም ሆነ ለእንስሳት አስተማማኝ መፍትሄ መገኘቱን የገለጹት ሃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት የንጹህ መጠጥ ውሃን በደጃቸው ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።
የአሚበራ ወረዳ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኢብራሂም መሐመድ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ለውሃ ፍለጋ የሚያደርገውን ረጅም ጉዞ በማስቀረት፣ በአቅራቢያው ንጹህ ውሃ አግኝቶ ተረጋግቶ እንዲኖር ማስቻሉን ገልጸዋል።
የዱለቻ ወረዳ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ መሐመድ ሷሊህ ማህበረሰቡ በተደጋጋሚ ይጠይቀው የነበረ የንፁህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ ከነእንሳሳቶቻቸው ጭምር ፕሮጀክቱ መመለስ መቻሉንና የነበረውን ዕጦት ማስወገዱን ተናግረዋል።