የኢትዮጵያን ገጽታ በራስ ስታቲስቲክስና እይታ መግለጽ የመረጃ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ገጽታ በራስ ስታቲስቲክስና እይታ መግለጽ የመረጃ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12 /2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ በራስ ስታቲስቲክስና እይታ መግለጽ መቻሉ የመረጃ ሉዓላዊነትን የማረጋገጫ ዋነኛ መንገድ መሆኑን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
''የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት'' በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው ሀገራዊ ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉባኤውን በይፋ በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ መረጃ የዚህ ዘመን ስትራቴጂካዊ ሀብት እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነባበት ቁልፍ የሉዓላዊነት ምሰሶ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተዋሰ አሊያም በውጭ አካላት ላይ ጥገኛ የሆነ መረጃ ሀገራዊ መሻታችንን ማሳካት ስለማያስችል፤ የፖሊሲ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የራስን መረጃ በራስ አቅም መሰብሰብ እና መተንተን ወሳኝ ግብዓት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ተቋማቸው የሀገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎችን በትክክል የሚያንጸባርቁ ስታቲስቲካዊ መረጃዎችን በስፋት በማመንጨት ላይ ይገኛል።
ተቋሙ በዋናነት ለውሳኔ ሰጪዎች፣ለእቅድና ለልማት ስትራቴጂዎች መንደፊያ የሚሆኑ ኦፊሴላዊ የስታቲስቲክስ መረጃዎችን በማመንጨት እንደሚታወቅም ጠቁመዋል።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በገንዘብና በባለሙያ ድጋፍ ስም መረጃዎቻቸው እንዳይቀለበሱና የራሳቸውን እውነታ በሌሎች እይታ እንዳያዩ የመረጃ ሉዓላዊነትን ማስከበር ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ከለውጡ ወዲህ የተመዘገቡት የኢኮኖሚ ሪፎርሞች እንዲሁም የሀገሪቱ የዲጂታላይዜሽን ፍጥነት እጅግ አስገራሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ እያሳየች ያለው ሁለንተናዊ እድገት የሰው ሀብት ልማት አቅሟንና የባለሙያዎቿን ክህሎት በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር መጥተው የሚማሩበትና የሚደመሙበት ደረጃ ላይ ደርሷል ነው ያሉት።
ይህንን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት በመጠቀም የሀገሪቱን ትክክለኛ ገጽታ በራስ ስታቲስቲክስና እይታ መግለጽ መቻሉ የመረጃ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ተቋሙ ለውሳኔ ሰጪነትና ለትንበያ ስራዎች የሚጠቅመውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና የሮቦቲክስ እድገትን በማጣጣም የዚህ ዲጂታል ለውጥ ተጠቃሚ መሆን መቻሉ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ትልቅ አቅም ያለው የሰርቨር መሠረተ ልማት መገንባት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ስጋቶችን ለመቀነስና መረጃዎችን በአንድ ቋት ብቻ ከመያዝ ለመውጣት በቴሌ ክላውድና በተለያዩ አማራጮች መረጃዎችን የማባዛት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ የክላውድ አማራጮች መረጃዎችን በተለያዩ አስተማማኝ ስፍራዎች አስቀምጦ ከመጠበቅ ባሻገር፣ ለአጠቃቀማቸው ጥብቅ የሆነ የደህንነት ጥበቃ እንደሚደረግላቸውም አረጋግጠዋል።