ቀጥታ፡

በድሬደዋ አስተዳደር ባለፉት አስር ወራት ከ17ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል

ድሬደዋ፣ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፡- በድሬደዋ ባለፉት አስር ወራት ከ17ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን የአስተዳደሩ ስራና ክህሎት ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፍጠሩንም ጠቁሟል።

በቢሮው የስራ ዕድል ፈጠራና የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰኢድ አሊ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ የስራ ዕድል ለመፍጠርና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ የተቀናጁ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል።

በአስተዳደሩ በተደረገው እንቅስቃሴም በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ከ17ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ለተመረቁ ወጣቶችና  የህብረተሰብ ክፍሎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ለተገኘው ውጤት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ  በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እየመጣ የሚገኘው እመርታ  ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በመጠቆም።

በተጨማሪም ግብርና፣ ኮንስትራክሽን እና የአገልግሎት ዘርፎች የስራ ዕድል የተፈጠረባቸው መስኮች መሆናቸውን አቶ ሰኢድ ገልጸዋል።

በአስተዳደሩ የሚገኙ የተማሩ ወጣቶችን ጥያቄዎች ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የመመለስ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አክለዋል።


 

እንደ አቶ ሰኢድ ገለፃ ቢሮው በዘንድሮ በጀት ዓመት  በስሩ በተደራጁት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በመታገዝ በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ድጋፎች አድርጓል።

የብድር፣ አጫጭር የሙያና የክህሎት ስልጠና እንዲሁም ከሚመለከታቸው ሴክተሮች ጋር በመቀናጀት የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች ማመቻቸቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ከ600 በላይ ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ የዕድገት ሽግግርን እንዲያፋጥኑ መሰራቱን አንስተዋል።

በስራ ዕድል ፈጠራውም ሆነ በገበያ ትስስር ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች ትኩረት ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም