በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ ተሳትፎ ማላቅ የሚያስችል ምህዳር ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ ተሳትፎ ማላቅ የሚያስችል ምህዳር ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018(ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ ተሳትፎ ማላቅ የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ ይሰጡበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጠቅላላ ምርጫ ውስን ቀናት ቀርተውታል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባም በተለያዩ ምዕራፎች በማካሄድና በማራዘም ከየካቲት 28 እስከ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።
መራጮችም በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊየን 514 በላይ ዜጎች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ ታዛቢነት ዕውቅና የተሰጣቸው 55 የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ከ60 ሺህ 277 በላይ ወኪሎችን አሰማርተዋል።
በመራጮች ትምህርት ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው 169 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ለመራጩ ህዝብ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ስልጠና እየሰጡ ይገኛል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በምርጫው ሂደት የሴቶች ወጣቶችና የአካል ጉዳተኞችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማረጋገጥ የሚያስችል ምኅዳር ተፈጥሯል።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ለመራጭነት የተመዘገበው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የዜጎችን ተሳትፎ በማሳደግ የአሳታፊነት አስቻይ ሀገራዊ አጀንዳ መፈጠሩን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሕገ-መንግሥታዊ የመምረጥና መመረጥ መብት የሚያረጋግጥ እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የምርጫ ሂደቱን ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊነት ለማስጠበቅ በተለያዩ አማራጮች ህዝብን የማንቃትና ማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ለአብነትም የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑና የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ የሚያልቅ ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።
በቀጣይም ለምርጫው ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊነት በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
በተለያዩ ሁኔታ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችም በምርጫው ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
ዜጎችም በወሰዱት የመራጭነት ካርድ መሠረት ለሀገር ይበጃል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ በመስጠት የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።