ቀጥታ፡

ታሪካዊው የዩሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ- ፍራይቡርግ ከ አስቶንቪላ በኢስታንቡል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12 /2018 (ኢዜአ)፦ በዩሮፓ ሊግ ፍራይቡርግ ከአስቶንቪላ ዋንጫውን ለማንሳት ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በቱርኪዬ ኢስታንቡል ከተማ በሚገኘው ቲውፕራሽ ስታዲየም ይካሄዳል።

በግማሽ ፍጻሜው አስቶንቪላ ኖቲንግሃም ፎረስትን በድምር ውጤት 4 ለ 1 በመርታት ለፍጻሜው ቀርቧል።

አስቶንቪላ ከ44 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ መድረክ ፍጻሜ ተመልሷል።

ፍራይቡርግ ከፖርቱጋሉ ብራጋ ጋር በነበረው ፍልሚያ በመጀመሪያው ጨዋታ 2 ለ 1 ተሸንፎ የነበረ ቢሆንም፣ ምሽት በሜዳው 3 ለ 1 በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአውሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ማለፉን አረጋግጧል።

በኡናይ ኤምሬ የሚመራው አስቶን ቪላ እ.ኤ.አ በ1982 የአውሮፓ ካፕ (የአሁኑ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ) ያነሳ ባለታሪክ ክለብ ነው።

አሰልጣኝ ኤምሬ በውድድሩ ላይ ለስድስተኛ ጊዜ ለፍጻሜ በመድረስ እና አራት ጊዜ ዋንጫ ማንሳታቸውን ተከትሎ "የአውሮፓ ሊግ ንጉስ" የሚል የክብር ስም ተሰጥቷቸዋል።

አሰልጣኙ አምስተኛ ዋንጫቸውን በማንሳት አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ሲዘጋጁ፣ በአንጻሩ ፍራይቡርግ በታሪኩ ምንም አይነት ትልቅ ዋንጫ አሸንፎ የማያውቅ በመሆኑ ይህ ጨዋታ ክለቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኩ ትልቅ ስኬት እንዲያስመዘግብ የሚያስችለው ታሪካዊ አጋጣሚ ሆኖለታል።

በፍራይቡርግ በኩል ተከላካዩ ሉካስ ኩብለር በግማሽ ፍጻሜው ያስቆጠራቸው ሁለት ወሳኝ ግቦች ለቡድኑ ስኬት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

በተጫዋቾች በኩል የሁለቱም ቡድኖች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ለዋንጫው ወሳኝ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከፍራይቡርግ በኩል አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ጣሊያናዊው ቪንቼንዞ ግሪፎ እና አራት ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ጃፓናዊው ዩይቶ ሱዙኪ ቁልፍ ተጫዋቾች ናቸው።

ከአስቶንቪላ በኩል አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ኦሊ ዋትኪንስ እና በግማሽ ፍጻሜው ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ድሉን ያረጋገጠው ካፒቴኑ ጆን ማክጊን የቡድኑ ዋና የማጥቃት ምንጮች ናቸው።

ጨዋታው በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረግ የመጀመሪያው ግንኙነት ነው።

በ36ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሊቨርፑልን 4 ለ 2 ያሸነፈው አስቶንቪላ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉን አረጋግጧል።

አስቶንቪላ የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ካነሰ እና በሊጉ አምስተኛ ሆኖ ካጠናቀቀ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ስድስት ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋሉ።

የ37 ዓመቱ ፍራንስዋ ሌቲክሲየር የፍጻሜውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የዩሮፓ ሊግ ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በመቀጠል ሁለተኛ አህጉራዊ የክለቦች ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም