ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሃዋሳ ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሃዋሳ ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ33ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ቡና በ43 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በ46 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል የራቁት ቡናማዎቹ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
በ32ኛ ሳምንት አዳማ ከተማን 3 ለ 1 የረታው ፋሲል ከነማ በድል ጉዞው ለመቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የሚደረገው መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሃዋሳ ከተማን ያገናኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ40 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሃዋሳ ከተማ በ45 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ32ኛ ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ከወጣበት ውጤት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና አከባቢ ፈቀቅ እንዲል ያደርገዋል።
ባለፉት ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሃዋሳ ከተማ የአሸናፊነቱን መንገድ ለማግኘት ይፋለማል።
ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሃዋሳ ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ሸገር ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ሸገር ከተማ በ40 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ በ31 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በ32ኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገደው ሸገር ከተማ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይጫወታል።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ያላሸነፈው መቀሌ 70 እንደርታ ማሸነፍ ወደ ድል ከመመለስ ባለፈ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
በዕለቱ የመጨረሻ መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ45 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በ34 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በ32ኛ ሳምንት በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 2 ለ 1 የተሸነፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።