ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2018 (ኢዜአ)፦‎ በ16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቱኒዚያን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ትናንት ማምሻውን በመሐመድ ስድስተኛ ስፖርት ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አሚር ሚስባህ በ93ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ አምበል ቢኒያም አብርሃ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።




ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በምድብ አንድ አራት ነጥብ በመያዝ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን ለዓለም ዋንጫ ወደ ሚያሳልፈው የማጣሪያ ጨዋታ አልፋለች። በዓለም ዋንጫው የመሳተፍ ተስፋዋም ቀጥሏል።

ቱኒዚያ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ከውድድሩ ተሰናብታለች።

በዚሁ ምድብ ማምሻውን በተካሄደ ጨዋታ አዘጋጇ ሞሮኮ ግብጽን 2 ለ 1 በማሸነፍ በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና በማጠናቀቅ ለሩብ ፍጻሜው ያለፈች ሲሆን ለዓለም ዋንጫ ማለፏንም አረጋግጣለች።

ግብጽ በአራት ነጥብ  ኢትዮጵያን በግብ ክፍያ በልጣ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ዓለም ዋንጫው አልፋለች።

16 ሀገራት እየተሳተፉበት በሚገኘው የአፍሪካ ዋንጫ በአራቱ ምድብ አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ ስምንት ሀገራት ቀጥታ ወደ ዓለም ዋንጫው ያልፋሉ።

ከየምድቡ ሶስተኛ የወጡ አራት ሀገራት ደግሞ በሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ቀሪ ሁለት አላፊ ቡድኖች ይለያሉ።

ኢትዮጵያ በጥሎ ማለፉ ማጣሪያ መንገድ ወደ ዓለም ዋንጫ ለመግባት ትፋለማለች።

የአፍሪካ ዋንጫው እስከ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

በአፍሪካ ዋንጫው ከሚሳተፉ 16 ሀገራት መካከል የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ 10 ሀገራት በጥቅምት እና ህዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።

በዓለም ዋንጫው 48 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም