የኢንዱስትሪ ፓርኩ መገንባት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ፓርኩ መገንባት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገር ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ በፖሊሲና በስትራቴጂ ከመደገፍ ባለፈ በተጨባጭ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ባሳለፍነው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ የተከፈተውን የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት፤ መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገር ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ በፖሊሲና በስትራቴጂ ከመደገፍ ባለፈ በተጨባጭ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው።
ፓርኩ በአምራች ዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን የመሥሪያ ቦታ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት የማይተካካ ሚና አለው ብለዋል።
አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅማቸውን ገንብተው ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪነት እንዲሸጋገሩ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ፓርኩ የተገነባበት ጥራትና የተሟላ መሠረተ ልማት የሀገር ውስጥ ምርትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያስችላል ሲሉ ገልፀዋል።
የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የገቢ ምርቶችን ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ለሀገር ዘላቂ ሉዓላዊነት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክት መገንባቱ ትልቅ ልምድና ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሌሎች አካባቢዎችም እንደ ማዕከልና አርዓያ ሆኖ እንደሚያገለግል አስገንዝበዋል።
በሁሉም አካባቢዎች ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና የሀገርን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፤ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኢንዱስትሪ ንቅናቄን እንደሚያግዝ ገልጸው፤ ይህም የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻን በማሳደግ ለኢንዱስትሪዎች ጠንካራ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።