በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአፍሪካ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመከላከል ሀገራት ቅንጅታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአፍሪካ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመከላከል ሀገራት ቅንጅታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአፍሪካ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመከላከል ሀገራት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ፀባይ ትንበያ ማዕከል ጋር በመተባበር ለሁለት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየውን 73ኛውን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ፀባይ አዝማሚያ ትንተናና ትንበያ ፎረም ተጠናቋል።
በፎረሙ የቀጣናው ሀገራት ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅት ተወካዮች እና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዚዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ሁለት ቀናት በአፍሪካ ቀንድ ዙርያ ያሉ የኢጋድ አባል ሀገራት ያለፈው የበልግና መጪው ክረምት ወቅት የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ ትንበያን አስመልክቶ ተወያይተዋል።
በዚህም ሁሉም ሀገራት ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የራሳቸውን የሜቲዎሮሎጂ መረጃዎችንና ከአካባቢያቸው አየር ሁኔታ በማገናዘብ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቅያ የሚሰጡበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸው አንስተዋል።
ከአየር ትንበያው በመነሳትም የሚኖረው የአየር ሁኔታ በግብርና፣በውሃ፣በጤና ላይ ሊያደርሰ የሚችለው አሉታዊና አዎንታዊ ተፅእኖ በመገምገም ለቀጣይ ዝግጅት የሚደረግበት መሆኑ ተናግረዋል።
እንዲሁም በህይወትና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የአደጋ ተጋላጭነትን ከመቀነስ አንፃር ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ መሰል መድረክ መዘጋጀቱ ጠቀሜታው የላቀ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ቀንድ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ አደጋዎች በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ እያደረሰ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ይህን ለመከላከል ሀገራት በቅንጅት መስራት አለባቸው ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ዋና ዳይሬክተር አብዲ ፊዳር (ዶ/ር) በአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የኢጋድ አባላት ሀገራት መረጃን መሰረት ያደረገ መረጃ በመለዋወጥ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳሰበዋል።