ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ገንቢ ሚና እየተወጡ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ገንቢ ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ገለጸ።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ነው።

በሕዝብና በመንግሥት መካከል ድልድይ በመሆን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ገንቢ ሚናቸውን የበለጠ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭና የምረጡኝ ቅስቀሳን በማቅረብ ዜጎች ግንዛቤን በመፍጠር በኩል እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችን የፖሊሲ አማራጭና የቅስቀሳ መርሃ ግብር ለህዝቡ በማስተጋባት በዕውቀትና ምክንያታዊነት የተመሰረተ የምርጫ ሂደት እንዲኖር አስቻይ ሁኔታ እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም እስከ ምርጫው ፍፃሜ ድረስ የሚጠበቅባቸውን አዎንታዊ ሚና በመወጣት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የተጣለባቸውን ድርብ ሀላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ምኅዳር ለማስፋት የተከናወኑ የሪፎርም እርምጃዎችም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያፋጥን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ወቅት የሚስተዋሉ ግድፈቶችንም በተቋማዊ አሰራር ሥርዓትና በኢትዮጵያ ሕግጋት መሠረት የእርምት እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም የህዝብን አንድነትና የሀገርን ዕድገት የሚያፋጥኑ መረጃዎችን በማፍለቅ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መፋጠን አዎንታዊ ሚና መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነገ “ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙኃን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ በሚያካሂደው የውይይት መድረክ ላይ፣ መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ወቅት ስለሚኖራቸው አስተዋጽኦ ሀሳቦች ይንሸራሸራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ምርጫን በተመለከተ የሚነሱ ሀሳቦች፣ በምርጫ ዘገባ ወቅት መገናኛ ብዙኃን ስለሚከተሏቸው መርሆዎች ሊዳስሱ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

ለምርጫው ስኬት ሲባል ጋዜጠኞች በምርጫ ዘገባ ሥነ-ምግባር፣ በግጭት አዘጋገብ እና በመረጃ ማጣራት (Fact-checking) ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት ይነሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር “ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት የመገናኛ ብዙኃን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ነገ የውይይት መድረክ ያካሂዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም