የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ለአካባቢው ልማት፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴና የንግድ መሳለጥ ትልቅ አቅም የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ለአካባቢው ልማት፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴና የንግድ መሳለጥ ትልቅ አቅም የሚሆን ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ) ፡- የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ለአካባቢው ልማት፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴና የንግድ መሳለጥ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተገለጸ።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ አሁናዊ ሁኔታን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ከተሳተፉት መካከል የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አበባው ግዛቸው፤ የአውሮፕላን ማረፊያው ለምስራቅ ጎጃም ዞንና አካባቢው ትልቅ ብስራት መሆኑን ገልጸዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው መገንባቱ የህዝቡን የዘመናት የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን አንስተው በተለይም ለቱሪዝም፣ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
በትራንስፖርት ዘርፉንም በማስፋት አከባቢውን ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ጋር በማገናኘት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።
ወይዘሮ ትግስት ልየው የተባሉ የጉብኝቱ ተሳታፊ በበኩላቸው እንደገለጹት የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው የህዝቡ የዘመናት ጥያቄ እንደነበር አውስተዋል።
"አሁን ላይ በእኛ እድሜ ተገንብቶ ማየታችን አስደሳች ነው" ያሉት ወይዘሮ ትግስት ይህም ወደ አዲስ አበባና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ ለመስራት መልካም እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ሌላው የጉብኝቱ ተሳታፊ አቶ ሙሉቀን አወቀ በበኩላቸው የደብረማርቆስ የውሮፕላን ማረፊያ መገንብቱ የአካባቢውን ልማት ከማፋጠን በተጨማሪ ምቾት ያለው ትራንስፖርት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
በጉብኝቱ ላይ የምሥራቅ ጎጃም ዞንና የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኖችና ከከተማው የተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።