ቀጥታ፡

የመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶች ለስፖርት ቱሪዝም እድገት ገንቢ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶች ለስፖርት ቱሪዝም እድገት ገንቢ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን "የስፖርት ቱሪዝም ለከተማችንና ለሀገራችን ያለው ፋይዳ" በሚል መሪ ሀሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ውይይት አካሒዷል።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ቢኒያም ታዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በመዲናዋ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና መሰረተ ልማቶች ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት ገንቢ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስፖርት ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን እድገት እያሳዩ ካሉ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዲስ አበባ ያሏትን መሰረተ-ልማት በመጠቀም ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመዲናዋ በርካታ ደረጃዎችን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማቶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡


 

የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ-ልማቶቹ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች እየተካሔዱባቸው መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ሁነቶቹ ለመዲናዋ የስፖርት ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ ማግኘት ያለባት ጥቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ማስፋፊያና ተሳትፎ ዳይሬክተር እንግዳወርቅ ዳንኤል በበኩላቸው፤ በመዲናዋ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ከተማዋን የዓለም አቀፍና አህጉራዊ የስፖርት ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ልማትና ማኔጅመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው ሙለታ (ዶ/ር)፤ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የስፖርት ቱሪዝም ዕድገት እንዲነቃቃ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የስፖርት መሰረተ ልማቶች ከተማዋን ውብ እና ጽዱ ከማድረግ ባሻገር ለስፖርት ቱሪዝም ማደግ ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል ያሉት ደግሞ የሆቴል ዘርፍ አሰልጠኝና አማካሪው ሰለሞን ታዬ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም