በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለግብርና ቴክኖሎጂ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለግብርና ቴክኖሎጂ ትኩረት ተሰጥቷል
ታርጫ ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልየግብርናውን ዘርፍ በምርምር በማስደገፍ የአርሶ አደሩን ሕይወት በመሠረታዊነት ለመቀየር የተጀመረው ሥራ ውጤታማ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በ137 ሚሊዮን ብር የተገነባውን የታርጫ ግብርና ምርምር ማዕከል ሕንጻን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለግብርና ቴክኖሎጂና ምርታማነታቸው የተረጋገጡ ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ተደርገዋል ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው የምርምር ማዕከልም የግብርናውን ዘርፍ በምርምር በማገዝ የአርሶ አደሩን ሕይወት በመሠረታዊነት ለመቀየር፣ አርሶ አደሩን የማሠልጠንና በምርምር የሚያወጣቸውን ምርጥ ዘሮች ተደራሽ ለማድረግ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ የመልማት አቅም በምርምር በማስደገፍ ውጤታማ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው።
ለዚህም የምርምር ማዕከላትን በሰው ኃይልና በግብዓት በማደራጀት ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረግ ጎን ለጎን ተደራሽነታቸው ላይ መሠራቱን ጠቅሰዋል።
ይህም ለአርሶ አደሮች በምርምር የወጡ የግብርና ማሳደጊያዎችን በማቅረብ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ከምግብ ፍጆታ አልፎ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች ላይ እንዲሳተፉ እንደሚያግዝም አስረድተዋል።
ምርታማነታቸው በማደጉም ራሳቸውን መጥቀምና አገርም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ኃይሌ በበኩላቸው፣ የማዕከሉ መገንባት ኢንስቲትዩቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ በሰብል፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በቀጥታ ወደ አርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ሚናውን የሚወጣ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ለሕንጻ ግንባታው አጠቃላይ ከ137 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ገልጸው፤ ማዕከሉ የጀመራቸውን ሥራዎች አስፍቶና አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ፣ የማዕከሉ መገንባት የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ለአካባቢው አርሶ አደር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።