ቀጥታ፡

በከተማው በለውጡ ዓመታት የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው

ገንዳ ውኃ፤ ግንቦት11/2018 (ኢዜአ)--በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ በለውጡ ዓመታት የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን የዞኑ መስተዳድር አስታወቀ።

የዞኑ መስተዳድር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል። 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ በዞኑ በለውጡ ዓመታት የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች መሰረት ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል። 

​"በገንዳ ውኃ ከተማም ሆነ እንደዞን የተገነቡና አሁንም በግንባታ ላይ ያሉ የልማት ሥራዎች የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የጤና፣ የትምህርት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንደሚጠቀሱም ተናግረዋል። 

በቀጣይም በተገባው ቃል መሰረት ተጨማሪ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት የአካባቢውን እድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል። 

​በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የአስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጥላሁን መኳንንት በበኩላቸው፤ በከተማዋ እየታዩ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው። 

​በአካባቢው ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን የተከናወኑ የልማት ሥራዎች በቀጣይ ዘላቂ ሰላምን በመገንባት ህዝቡን ከዚህም በላይ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ማሳያ ናቸው ብለዋል። 

የተጀመሩ የተቋማት ግንባታ ሥራዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም አረጋግጠዋል።

​የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪ  አቶ አስቻለው ጋሻው በበኩላቸው ቀደም ሲል በከተማዋ የነበሩ የመሰረተ ልማት እጥረቶች በለውጡ ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ገልጸዋል። 

​በተለይም የአካባቢውን ሀብት በጥሬ እቃነት የሚጠቀም የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ግንባታ ለአልሚ አርሶ አደሮችና ለሥራ ፈላጊ ወጣቶች ከፍተኛ ጥቅም የሰጠ መሆኑን አብራርተዋል። 

"የአካባቢያችን ሰላም በዘላቂነት በመጠበቅ ልማቱ እንዲፋጠንና ተጠቃሚነታችን እንዲያድግ የበኩላችንን እንወጣለን"  ብለዋል። 

በእለቱ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ፣ አዲስ የተገነቡ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ፣ ሆቴል፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የአሚኮ ምዕራብ ጎንደር ቅርንጫፍ ግንባታና ሌሎች ተቋማት ተጎብኝተዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም