ቀጥታ፡

በዞኑ የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እየተጠናቀቁ ነው

ጭሮ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እየተጠናቀቁ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኢክራም ጠሀ ገለጹ።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ እና ሐዊ ጉዲና ወረዳዎች 950 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ተቋማት በክልልና በዞን ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ተመርቀዋል።


 

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ዋና አስተዳዳሪዋ ወይዘሮ ኢክራም ጠሀ እንዳሉት፤ መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር በመለወጥ ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

የልማት ተቋማቱን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ የሕብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።


 

ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል በሐዊ ጉዲና የአርብቶ አደር ወረዳ ከ890 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ የንጹሕ ውኃ ተቋም አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጥና የአርብቶ አደሩን እንስሳት የውኃ አቅርቦት ፍላጎት የሚያሟላ በመሆኑ፣ የዘመናት ጥያቄን መመለስ የቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሌላው በጭሮ ወረዳ የተገነባው የመረዋ ድልድይ የአካባቢውን አርሶ አደሮች የትራንስፖርትና የቁልፍ መገናኛ ችግር ለመፍታት ታስቦ ግንባታው መከናወኑንም ጠቅሰዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አሰፋ በበኩላቸው፤ መንግሥት የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት በማሟላት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሠራቸው ሥራዎች እጅግ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ከመመለስ ባለፈ፣ ለልማት ፕሮጀክቶች ፍጥነትና ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አመልክተዋል።

የዞኑ አስተዳደርም የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች በየደረጃውና በፍጥነት ለመመለስ የሚያደርገውን የተቀናጀ ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም