ቀጥታ፡

የአማራ ክልልን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)

ወረባቦ፤ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፡- የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን የማጠናከር ተግባር እንደሚቀጥል የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።

በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ከ543 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ 52 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፣ የክልሉን ሰላም በማስጠበቅና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማስቀጠል ኢትዮጵያን ተምሳሌት ሀገር የማድረጉ ተግባር ይጠናከራል።


 

በዚህም በለውጡ መንግስት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ የመፈጸም ብቃት ማደግ ህብረተሰቡን ፈጣን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሮችን ወደ እድልና ድል በመቀየር በልማት ስራው አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመው፤ በክልሉ አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመሆን እያሰፈነ ያለው ሰላምና ልማት እያረጋገጠ ነው ብለዋል።

ለክልሉ ሰላቂ ሰላምና ልማት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ጭምር በቅንጅት መስራት መቻሉ የመንግስትን አቃፊነትና አሳታፊነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ በበኩላቸው፣ በክልሉ ለማህበራዊ ተቋማት ተደራሽነት የተሰጠው ትኩረት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በዚህም በጤናና ትምህርት ዘርፎች ህብረተሰቡን በተጨባጭ ተጠቃሚ በማድረግ አበረታችና ተስፋ ሰጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮነን በበኩላቸው፣ ከህብረተሰቡ ጋር የዞኑን ሰላም ማስጠበቅ መቻሉ ለሚካሄዱ የልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስችሏል።

በዚህም በዞኑ የ110 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታን በአጭር ጊዜ በጥራት ማጠናቀቅ መቻሉን አመላክተዋል።


 

በዛሬው እለት ብቻ በ543 ሚሊየን ብር የተገነቡ 52 የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች መመረቃቸውን በማሳያነት አቅርበዋል።

በተገነቡት መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ በመሆናቸው ተደስተናል ያሉት ደግሞ የወረባቦ ወረዳ ነዋሪዎች አቶ መሀመድ ሀሰን እና አቶ ይማም መሀመድ ናቸው።

በተለይ በአጭር ጊዜ ግንባታቸው ተጠናቆ ዛሬ የተመረቁ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ኬላዎች፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ አድርገውናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም