ቀጥታ፡

በዞኑ በመኸር ወቅቱ በመካናይዜሽን ለታገዘ ኩታ ገጠም እርሻ ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ፣ ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በመኸር ወቅቱ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ  በመካናይዜሽን ለታገዘ ኩታ ገጠም እርሻ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

በዞኑ ለምርት ወቅቱ የሚያስፈልግ የምርት ማሳደጊያ ግብአትም በወቅቱ እየተሰራጨ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

የእርሻ መካናይዜሽን የጉልበት ሥራን በሚተኩ እንደ ትራክተርና ኮምባይነር ባሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና ማሽኖች ግብርናን ማዘመን ሲሆን አሰራሩም ጊዜን፣ ጉልበትና ወጪን በመቀነስ የምርት መጠንንና ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ነው።

በዚህም መንግስት በሀገሪቱ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የመካናይዜሽን እርሻን በስፋት ለመጠቀም ግብ ጥሎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ በምስራቅ ሸዋ ዞን የ2018/19 ምርት ዘመን የመኸር ወቅት እርሻ ገጽታ በተመለከተ ከዞኑ  ግብርና ፅህፈት ቤት  ምክትል  ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ጋር ቆይታ አድርጓል ።

አቶ አብነት እንደገለጹት በዞኑ በመኸር ወቅቱ 512 ሺህ 622 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በምርት ወቅቱ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ  በመካናይዜሽን ለታገዘ ኩታ ገጠም እርሻ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በዚህም በምርት ወቅቱ አጠቃላይ ከሚለማው መሬት ውስጥ ከ410 ሺህ ሄክታር በላይ  በኩታ ገጠም እንደሚለማ ገልፀው እስካሁን ድረስ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በትራክተር በመታገዝ መታረሱን ተናግረዋል።

በዞኑ ከሚያዚያ 2018 ዓ.ም መጨረሻ አንስቶ የአገዳ ሰብሎችን መዝራት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው በሰኔ 2018 ዓ.ም ደግሞ የብርእ ሰብሎች በስፋት እንደሚዘሩ አመልክተዋል።

በመኸር ወቅት እርሻው ከ195 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰው በምርት ወቅቱ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ  የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አውስተዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አስራት ጌቱ በበኩላቸው በምርት ዘመኑ ለዞኑ ከሚያስፈልገው  አንድ ሚሊዮን  ኩንታል በላይ  ዳፕና ዩሪያ ማዳበሪያ ውስጥ ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው መቅረቡን ተናግረዋል።


 

እስካሁን ድረስ 537 ሺህ  ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ  በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ጠቁመው አርሶ አደሮችም  ማዳበሪያን በመጠቀም  የግብርና ስራቸውን እያሳለጡ ይገኛሉ ብለዋል።

በተጨማሪም ጤፍና ስንዴን ጨምሮ ከ68 ሺህ ኩንታል በላይ  ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም