ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ እስካሁን ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል-ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ እስካሁን ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቷል-ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ግንቦት 11/2018 (ኢዜአ)፦ለዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኝ የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ተፅዕኖን በመቀነስና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ዘርፈ-ብዙ ፋይዳዎችን እያስገኘ ይገኛል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሀገር በቀል እጽዋቶችንና የተፈጥሮ ሀብቶችን ከመጠበቅ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመከላከልና የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግስት የተለያዩ ተግባራትን ከማከናወን አንጻር ግንባር ቀደም ለውጥ አስገኝቷል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት በተሰሩት ስራዎች አበረታች ውጤት የተመዘገበ ሲሆን፤ በመርሃ-ግብሩ 48 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን አረንጓዴ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ልማት ከተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ባለፈ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን የሰነቀ ሲሆን የአየር ንብረት ተጽዕኖን በመቀነስ ለኢትዮጵያ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ መስኮች ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ እያስገኘ ይገኛል፡፡
ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ላይ የተከናወኑ ሥራዎችና የተመዘገቡት አበረታች ውጤቶች ትልቅ ምስክር ናቸው፡፡
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሁለተኛው ምዕራፍ ማጠናቀቂያ መሆኑን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ቀደም ሲል ከነበሩ የአረንጓዴ አሻራ አፈጻጸሞች የተወሰዱ ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ የዘንድሮው ዕቅድ በቁጥር ደረጃ ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም መሠረት 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ሰፊ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንና አሁን ላይ ለተከላው የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙ ጠቁመው የስነ-ምህዳር ሁኔታን መሠረት ያደረገ የችግኝ ዝርያዎች መረጣ መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ችግኝ የሚተከሉባቸው ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ሥራ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አሁን ላይ በበርካታ ዜጎች ዘንድ ባህል እየሆነ መምጣቱንና የተሳታፊዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አንድነት በተግባር የሚረጋገጥበት ትልቅ አገራዊ ኩነት በመሆኑ፣ መላው ሕዝብ በኃላፊነት ስሜትና በቀዳሚነት እየተሳተፈበት ይገኛል ብለዋል።
ለዘንድሮው የችግኝ ዝግጅት ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል 40 በመቶው ሀገር በቀል የደን ዛፎች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቅሰው፣ 60 በመቶው ደግሞ ለምግብ ዋስትናና ለሌሎች ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች የሚውሉ የፍራፍሬና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መሆናቸውን አስረድተዋል።